የቀድሞ የደቡብ ፖሊስ እና የደደቢት እንዲሁም በፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ህይወቱ የደቡብ አፍሪካዎቹን ቢድቬስት ዊትስ እና ፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ ያሳለፈው የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቹ ጌታነህ ከበደ (ሰበሮ) በዛሬው ዕለት ለ2 ዓመት ፈረሰኞቹን ተቀላቅሏል።
ጌታነህ ደደቢት ቡድኑን በአዲስ መልክ ለማደረጀት፤ በአነስተኛ ክፍያ ወጣቶች ላይ ትኩረት ለማድረግ ውሳኔ ካስተላለፈ በኋላ በተለያዩ ክለቦች ሲፈለግ ቆይቶ በመጨረሻ ፈረሰኞቹን ተዋህዷል፡፡
የ26 አመቱ ተጫዋች ዲላ ከተማ የተወለደ ሲሆን 1.72 ሜትር ይረዝማል፡፡ በደቡብ ፖሊስ ጥሩ ብቃት ማሳየቱን ተከትሎ ወደ ደደቢት አምርቷል፤ ከክለቡም ጋር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ድልን አጣጥሞ፤ወደ ደቡብ አፍሪካ ጉዞውን አድርጎ እንደገና በመመለስ ደደቢትን ባለፉት ሁለት የውደድር ዓመታት አገልግሏል፤ በተለይ ባለፈው አመት የፕሪምየር ሊግ ወድድር በ25 ግቦች የሊጉ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ለ16 አመታት የቆየውን የዮርዳኖስ አባይን ክብረወሰን መስበሩ ይታወሳል፡፡