ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ እቃዎችን ማምረት ካልጀመረች የውጭ ምንዛሬ እጥረቷን ልትፈታ አትችልም ተባለ፡፡ የዉጭ ምንዛሪ እጥረቷን ለመፍታት ድሮን ቴክኖሎጂ፣ አውቶሞቲቭ ኢንደስትሪ እና የህክምና እቃዎች ማምረት ይኖርባታልም ተብሏል፡፡
ይህ የተባለዉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ
በኢትዮጵያ የታንዛኒያ አንምባሳደር ከሆኑት ቼንግሬ ሚካማን ጋር በምስራቅ አፍሪካ የቴክኖሎጂ ማበልፀጊያና ማምረቻ ለማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በመከሩበት ወቅት ነዉ።
ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በድረ ገጹ እንዳስታወቀዉ ኢትዮጵያ በ2009 ዓ.ም ብቻ እንኳን ከወጪ ንግድ 3ቢሊየን ዶላር ብታገኝም ለገቢ ንግድ ደግሞ 15 ቢሊየን ዶላር አውጥታለች።
ከገቢ ንግዱ ውስጥ ከ85 በመቶ በላይ ለቴክኖሎጂ ውጤቶች መግዣ የወጣ ነው ያሉት ሚኒስትሩ እነዚህን የቴክኖሎጆ ምርቶች ቢቻል በሀገር ውስጥ ካልሆነም በቀጠናው ማምረት ካልተቻለ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን መቅረፍ አይቻልም ብለዋል።
በቀጣይ በምስራቅ አፍሪካ የቴክኖሎጂ ማምረቻና ማበልፀጊያ ለማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮችና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሮች ጋር ሰፊ ውይይቶች ይደረጋሉ ተብሏል።