በአገር አቀፍ ደረጃ ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሆናቸው ልጃገረዶች በመደበኛነት የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባትን ከጥቅምት 2011 ዓ.ም ጀምሮ በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ተቋማትና በሚዘጋጁ ጊዜያዊ የክትባት ማዕከሎች ሊሰጥ መሆኑን የፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በድረገጹ አስታዉቋል፡፡
የፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተወካይ አቶ አስናቀ ዋቅጅራ የማህጸን በር ካንሰር በሽታ በአገራችን ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በስፋት በወሊድ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ሴቶችን በገዳይነቱ የሚታወቅ በሽታ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በዓለም ላይ ከ200 በላይ የካንሰር አይነቶች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፤ ከነዚህ ውስጥ የማህጸን በር ካንሰር አንዱ ነው፡፡
በኢትዮጵያም በየዓመቱ በበሽታው የሚጠቁ ሰዎች ብዛት ከ4600 በላይ የሚደርስ ሲሆን በበሽታው ከተጠቁት ውስጥም ከ3200 በላይ እንደሚሞቱ አቶ አስናቀ ገልጸዋል፡፡