አርትስ 02/02/2011
ከሁለት ሳምንት በፊት ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የደረሰውና “በራሪ የአይን ሆስፒታል” ተብሎ የሚጠራው የኦርቢስ አውሮፕላን ውስጥ ስልጠናና ህክምና እየተሰጠ ነው።
ዓለም በደረሰበት ዘመናዊ የዓይን ህክምና መሳሪያዎች የተደራጀ መሆኑ የሚነገርለት የኦርቢስ በራሪ ሆስፒታል የአይን ህክምና አገልግሎትን ለማስፋፋት እና የአቅም ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ በየዓመቱ ወደታዳጊ ሃገራት ይጓዛል።
45 አባላት ያሉት አንድ ዓለምአቀፍ የሃኪሞች ቡድን ይዞ ለአምስተኛ ጊዜ ወደኢትዮጵያ በመጣው በዚሁ አውሮፕላን ውስጥ ባለፉት 2 ሳምንታት ብቻ 44 ኢትዮጵያውያን ሃኪሞች በተግባር የተደገፈ ስልጠና ማግኘታቸውን የተቋሙ ህክምና አገልግሎቶች ምክትል ሃላፊ ዴቪድ ሃንተር ለአርትስ ቲቪ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ለ250 ኢትዮጵያውያን ህክምና የተሰጠ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 120 የሚሆኑት የከፋ ግላኮማ እና ሌሎች ከባድ የዓይን በሽታዎች ቀዶ ህክምና አገልግሎት ማግኘታቸውንም ጠቁመዋል።
ህክምናው እና ስልጠናው በ10 ዓይነት የዓይን በሽታዎች ላይ አትኩሮ እየተሰጠ መሆኑን የተናገሩት ዴቪድ ሃንተር ይህም ዓለም የደረሰበትን የህክምና ዕውቀት ለኢትዮጵያውያን ሃኪሞች ለማስተላለፍ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል ብለዋል።
የዘንድሮው የኦርቢስ በራሪ የአይን ሆስፒታል አውሮፕላን ወደኢትዮጵያ መምጣት ምክንያት ድርጅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎት መስጠት የጀመረበትን 20ኛ ዓመት እያከበረ ከመሆኑ ጋር የሚያያዝ መሆኑም ታውቋል።