በሰሜን ወሎ ዞን ላሊበላ ከተማ በአንድ ግለሰብ በተተኮሰ ጥይት የሟቾች ቁጥር ዘጠኝ ደረሰ
አርትስ 26/02/2011
በላሊበላ ከተማ ሮሀ ቀበሌ ወርቅ ድንጋይ ተብሎ በሚጠራው መንደር ቅዳሜ ምሽት 2፡40 ገደማ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ዘጠኝ ሰላማዊ ሰዎችን የገደለው ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን የላሊበላ ከተማ ከንቲባ አቶ ሀብታሙ ማሞ ለአርትስ ቲቪ ገልፀዋል፡፡ አቶ ሀብታሙ እንዳሉት ግለሰቡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላሊበላ ቅርንጫፍ ጥበቃ ሰራተኛ ሲሆን ለስራ በተሰጠው መሳሪያ ፀብም ሆነ ሌላ ግንኙነት የሌላቸውን ግለሰቦች ከመንገድ ጀምሮ በመተኮስ መግደሉን እና በአንድ መጠጥ ቤት በመግባት ባለቤት የሆነችውን ግለሰብ መግደሉ ታውቋል ፡፡
ወዲያውኑ ስምንት ሰዎች ሲሞቱ አሁን የሟቾች ቁጥር ዘጠኝ መድረሱ ታውቋል፡፡ የቆሰሉት ሰዎች በደሴ ሪፈራል ሆስፒታል እና በወልዲያ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን የገለፁት ከንቲባው ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡