ግብፅ ሴቶች በአደባባይ ፊታቸውን ሸፍነው እንዳይንቀሳቀሱ ልትከለክል ነው
አርትስ 26/02/2011
የግብፅ ፓርላማ ሴቶች ፊታቸውን ኒቃብ በተባለ ልብስ ሸፍነው ህዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ እንዳይንሳቀሱ የሚከለክል የህግ ረቂቅ ለውሳኔ አቅርቧል፡፡
የግብፅ የፓርላማ አባሏ ጋዳ አጃሚ ለግብፅ ስትሪትስ ሲናገሩ ይህን የምናደርገው በሀገራችን እየተስፋፋ የመጣውን የሽብር ወንጀል ለመከላከል በማሰብ ነው ብለዋል፡፡
አጂሚ አክለውም ሴቶች ፊታቸውን የሚሸፍኑበትን ልብስ ወንዶች ለብሰውት በቀላሉ ወንጀል ይሰሩበታል፤ እናም ይህን ወንጀል ለመቀነስ ከዚህ የተሸለ አማራጭ የለንም ነው ያሉት፡፡
አዲሱ ረቂቅ ህግ ይህን ተላልፈው በተገኙ ሴቶች ላይ አንድ ሺህ የግብፅ ፓውንድ ቅጣት እንደሚደነግግም ተነግሯል፡፡
የግብፅ ህገ መንግስት ዜጎቹን ከየትኛውም ጥቃት እንዲጠበቁ ከለላ ሰጥቷቸዋል ያሉት የፓርላማ አባሏ ፊት መሸፈን የሀይማኖታዊ ህግ አካል አይደለም ይልቁንም ሴቶች ማንነታቸውን እንዲደብቁ እስልምና አያበረታታም ብለዋል፡፡