አርትስ 28/02/2011
ጥቅምት 30 ሊወጣ የነበረዉ የ20/80 እና የ40/60 የጋራ መኖርያቤቶች ዕጣ መራዘሙን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ጋሻው ተፈራ እንደገለፁት ፤በዚህ ዓመት ግንባታቸው ከተጠናቀቁት ከ94 ሺህ በላይ ቤቶች ውስጥ 21 ሺው የ 20 /80 ቤቶች ሲሆኑ፤ ከተገነቡት 38 ሺህ ቤቶች ውስጥ ደግሞ 17 ሺዎቹ በ 40/60 እጣ ውስጥ ተካተው ነበር ብለዋል፡፡
አንደ ሃላፊው ገለፃ በአጠቃላይ በ 20 /80 እና በ40/60 የቤት ፕሮገራሞች በዚህ ዓመት ለተጠቃሚ ይደርሳሉ ተብሎ ከታቀደው 132 ሺህ ቤቶች ውስጥ 42 ሺ 341 የሚሆኑት ከ80 በመቶ በላይ ግንባታቸው የተጠናቀቁ እና ለተጠቃሚዎች መሰጠት የሚችሉ ናቸው ብለዋል፡፡
ነገር ግን ከዚህ ቀደም የነበረውን የአሰራር ሂደት ፣በኢንሳ እና በንግድ ባንክ ተይዞ የነበረውን ሲስተም አስተዳደሩ በራሱ ሃላፊነቱን ተረክቦ የራሱን አሰራር በመዘርጋት ላይ በመሆኑ ምክንያት እጣው እንደተራዘመ ነው የተገለፀው፡፡
በዚህም መሰረት እስከ ሰኔ 30 2011 ዓ.ም በእቅድ የተያዙትን እና የ1997 ተመዝጋቢዎችን ቤት አጠናቆ ለተጠቃሚዎች እንደሚያስረክብ ጽህፈት ቤቱ የገለፀ ሲሆን፤ የኮዬ ፈጬ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግን 2 አመታትን እንደሚወስዱ አስታውቋል፡፡
በተያያዘም በቅርቡ የተጀመረው ለመንግስት ሰራተኞች በኪራይ የሚተላለፉ 1 ሺህ 718 ቤቶች ግንባታ አጠናቆ እንደሚያስረክብ ነው አቶ ጋሻው የተናገሩት፡፡