ክልሉ ህገወጥ ወታደራዊ ስልጠና ሲወስዱ የተያዙ ግለሰቦችን ተሃድሶ ስልጠና ሰጥቶ ለቀቀ
አርትስ 29/02/2011
ከአንድ ወር በፊት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሶሳ ወረዳ ጫካ ውስጥ ህገ-ወጥ ወታደራዊ ስልጠና ሲወስዱ የተያዙ 51 ሰዎች ተሃድሶ ተሰጥቷቸው መለቀቃቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ሰይፈዲን ሃሩን እንዳሉት በተካሄደው አሰሳ በተጨማሪ ሰዎች መያዛቸውን ተከትሎ በድርጊቱ የተሳተፉ ግለሰቦችች ቁጥር 83 ደርሶ ነበር።
የተያዙት ሰዎች ዕድሜያቸው ከ13 እስከ 26 ዓመት የሚሆን ታዳጊና ወጣት ተማሪዎች የነበሩ ሲሆን “በውጪ አገር የሥራ ዕድል እንፈጥርላችዋለን” በሚል የተሳሳተ ቅስቀሳ ተታለው የተወሰዱ ናቸው ብለዋል ኮሚሽነሩ።
በፖሊስና በክልሉ አመራሮች ለ10 ተከታታይ ቀናት የተሰጣቸውን ተሃድሶ ስልጠና በማጠናቀቃቸውም መለቀቃቸውን ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡
” ወጣቶቹ በወሰዱት የተሃድሶ ስልጠናም የተከተሉት መንገድ የተሳሳተ፣ ህገ-ወጥና ራሳቸውንም ሆነ ህዝቡን አደጋ ውስጥ ሊጥል የሚችል መሆኑን በጥልቀት ተረድተዋል” ብለዋል ኮሚሽነር ሰይፈዲን፡፡
እስካሁን በህገ-ወጥ ወታደራዊ ስልጠናው 11 ሰዎች በአሰልጣኝነት ተሳትፈዋል በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታውቋል፡፡
ኮሚሽነር ሰይፈዲን እንዳሉት ተጠርጣሪዎቹ ራሱን የበርታ ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ (በህነን) በሚል የሚጠራው ቡድን አባላት ሲሆኑ ካሳ አልተከፈለንም በሚል ያኮረፉ ናቸው ።
ህገ-ወጥ ወታደራዊ ስልጠናውን ሲሰጡ የነበሩ ግለሰቦችን ክልሉ በምንም መልኩ አይታገስም ያሉት ኮሚሽነሩ እነዚህን አካላት ለህግ ለማቅረብ እየሰራን ነው ብለዋል።ዜናው የኢዜአ ነው።