የመንግስት ኃላፊዎች ወደተማሩባቸው ትምህርት ቤቶች እየሄዱ ልምዳቸውን ሊያካፍሉ ነው
አርትስ 30/02/2011
ትምህርት ሚኒስቴር ያዘጋጀውና ተማሪዎች ከተለያዩ ግለሰቦች መልካም ተሞክሮ ይቀስሙበታል የተባለ መርሃ ግብር እስከ ህዳር 26 ድረስ ይካሄዳል ተባለ።
“የዓለም ታላቁ የትምህርት ቀን” የሚል መጠሪያ በተሰጠው መርሃ ግብር በተለያዩ መስኮች ውጤታማ የሆኑ ግለሰቦች ወደተማሩባቸው ትምህርት ቤቶች በመሄድ የህይወት ተሞክሯቸውን ለተማሪዎች ያካፍላሉ ተብሏል።
ግለሰቦቹ መልካም ተሞክሯቸውን ከ5ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች እንደሚያጋሩ ነው በትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ወይዘሮ ሐረጓ ማሞ የተናገሩት።
በተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊነቶች ላይ ያሉ ግለሰቦችም ወደተማሩባቸው ትምህርት ቤቶች በመሄዱ ለተማሪዎች ስለተሞክሮዎቻቸው በክፍል ውስጥ ለ45 ደቂቃና በመሰብሰቢያ ቦታዎች ተገኝተው ገለፃ ያደርጋሉ ተብሏል።
አቅሙ ያላቸው ግለሰቦች ወደየትምህርት ቤታቸው ሲሄዱ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያግዙ የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያበረክቱም ተመክረዋል።
በየዓመቱ የሚከበረው “የዓለም ታላቁ የትምህርት ቀን” በ2030 ድህነትን ከዓለም የማጥፋት እና ጸረ አብሮነትና ኢ-ፍትሃዊነትን የመዋጋት ዓላማ ያነገበ መሆኑን ኃላፊዋ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ተማሪዎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እንዲሁም የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት እገዛ እንዲያደርጉ የሚያዘጋጅ ስራ የሚሰራበት ነው ተብሏል።
ለአንድ ወር ያህል በሚቆየውና የፊታችን ሰኞ በሚጀምረው የዓለም ታላቁ የትምህርት ቀን አማካኝነት ከአንድ ሺ በላይ ትምህርት ቤቶች በቀድሞ ተማሪዎቻቸው ይጎበኛሉ።