ተጠባቂው የማንችስተር ዩናይትድ እና አርሰናል ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ
አርትስ ስፖርት 27/03/2011
በ15ኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ትናንት ምሽት ስድስት ያህል ጨዋታዎች የተከናወኑ ሲሆን በጉጉት በተጠበቀው የኦልድትራርድ የማንችስተር ዩናይትድ እና አርሰናል ጨዋታ በ2 ለ 2 አቻ ውጤት ተጠናቅቋል፡፡
አርሰናሎች ቅድሚያ የማስቆጠር ዕድል ያገኘው በ26ኛው ደቂቃ በተከላካዩ ሽኮድራን ሙስጣፊ ሲሆን የግብ ጠባቂው ዳቪድ ዴህያ ስህተት ደግሞ ለጎሏ መቆጠር አስተዋፅኦ ነበረው፤ አንቶኒ ማርሽያል ከአራት ደቂቃ በኋላ ዩናይትድን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ማርኮስ ሮሆ በራሱ ግብ ላይ ግብ አስቆጥሮ መድፈኞቹ በድጋሚ መምራት ቢችሉም ሊንጋርድ ኳስን ከመረብ አገናኝቶ ጨዋታው በሁለት አቻ እንዲጠናቀቅ ሁኗል፡፡ አርሰናሉ በ20 ተከታታይ ጨዋታ ያለመሸነፍ ጉዞውን ገፍቶበታል፡፡
በምሽቱ ሊቨርፑል ወደ ከበርንሊ ተጫውቶ 3 ለ 1 ሲረታ ጃክ ኮርክ በርንሊን መሪ ቢያደርግም በሚልነር፣ ፊርሚኖ እና ሻኪሪ ግቦች አሁንም ቀያዮቹ በፕሪምየር ሊጉ ያለመሸነፍን አስቀጥለዋል፡፡
በሞሊኒክስ ወልቨርሃምፕተን ደግሞ ቼልሲን 2 ለ 1 ሲያሸንፍ ጂሜኔዝና ጆታ ለባለሜዎቹ ሎፍተስ ቺክ ደግ ለሰማያዊዎቹ ኳስን ከመረብ አዋህደዋል፡፡
ቶተንሃም በዊምብሊ ሃሪ ኬን፣ ሉካስ ሞራና ሰን ሂንግ ሚን ጎሎች 3 ለ 1 ድል አድርጓል፡፡ ኢቨርተን ከ ኒውካስል፤ ፉልሃም ከ ሌስተር ሲቲ በአንድ አቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡
ሊጉን ማንችስተር ሲቲ በ38 ነጥቦች ሲመራ ሊቨርፑል በ39 ነጥብ 2ኛ፤ ቶተንሃም በ33 ነጥብ 3ኛ፣ ቼልሲና አርሰናል ደግሞ በእኩል 31 ነጥቦች በግብ ክፍያ ተበላልጠው 4ኛ እና 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡