የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ፎረም እንዲቋቋም ተወሰነ
አርትስ 27/03/2011
በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ፎረም እንዲቋቋም ከውሳኔ ላይ መድረሱ ተገለፀ።
የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ)፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አመራሮች በጋራ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው ይህ የተገለፀው።
የጋራ መግለጫውንም የኦዲፒ ምክትል ሊቀ መንበርና የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ፣ የኦፌኮ ሊቀ መንበር ዶክተር መረራ ጉዲና እና የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ናቸው የሰጡት።
ፋና እንደዘገበዉ በመግለጫቸውም የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ፎረም እንዲቋቋም መወሰኑን ያስታወቁ ሲሆን፥ የፎረሙ መቋቋምም በየጊዜው ተመሳሳይ ውይይት ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።
በፓርቲዎች መካከል ችግር ካጋጠመም ችግሩን በመደማመጥ እና በውይይት ለመፍታት የሚያስችል መሆኑንም ነው ያስታወቁት።
የኦዲፒ ምክትል ሊቀ መንበርና የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ በመግለጫቸው አክለውም፥ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየሰራ መሆኑን በመግለጽ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ህዝቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ኦሮሚያ ክልልን የብጥብጥ አውድማ ለማድረግ ሴራዎች እየተጠነሰሱ መሆኑን
የገለጹት አቶ ለማ፥ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይሁን ህዝቡ ይህንን በንቃት መመልከት እንዳለበት መልእክት አስተላልፈዋል።
እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ደግሞ ከሌሎች ጊዜያት በተለየ መልኩ በጋራ መቆም ወሳኝ መሆኑንም ነው ያስታወቁት።
የኦፌኮ ሊቀ መንበር ዶክተር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፥ አሁን የተመዘገበው ድል በእልህ አስጨራሽ መሰዋእትነት የተገኘ በመሆኑ፤ የወጣቱ እና የህዝቡ እንድነት መጠናከር አለበት ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችም የህዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ አንድነታቸው መጠናከር አለበት ያሉት ዶክተር መረራ፥ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለው ልዩነትም በውይይት መፈታት እንዳለበት ገልፀዋል።
የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳም፥ የህዝብን ችግር መቅረፍ የሚቻለው አንድነትን በማጠናከር እንደሆነ በመግለጫው ላይ ተናግረዋል።
መዋሃድ የሚችሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲዋሃዱ፤ መዋሃድ የማችሉ ደግሞ እርስ በእርስ በመተባበር የህዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ በጋራ መስራት ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።