ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከ28 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተገኘ
አርትስ 04/04/2011
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለሱዳንና ጅቡቲ ካቀረበው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከ28 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን የተቋሙ የማርኬቲንግና ቢዝነስ ዲቨሎፕመንት ቢሮ አስታውቋል፡፡
ገቢው የተገኘው ከሰኔ 2010 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 2011 ዓ.ም ባሉት አምስት ወራቶች ውስጥ ነው፡፡
ጅቡቲ ከ17 ሚሊየን ዶላር በላይ የኃይል ግዥ በመፈፀም ከፍተኛውን ድርሻ የምትወስድ ሲሆን ቀሪው ደግሞ ከሱዳን የተገኘ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በ2010 በጀት ዓመት ለሱዳንና ጅቡቲ ካከናወነችው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከ75 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘቷ ይታወሳል፡፡
ሃገሪቱ ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል በማልማት በምስራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር በስፋት እየሰራች ሲሆን ለጅቡቲና ሱዳን በዓመት በአማካኝ ከ150 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ ላይ እንደምትገኝ ቢሮው ገልጻል፡፡
ሌሎች የአፍሪካ ሃገራትም ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ኃይል ካላት እምቅ አቅም ለመጠቀምና የሁለትዮሽ የኃይል ትስስር ግንኙነት ለመጀመር ፍላጎት ከማሳየት ባሻገር ወደ ስምምነት እየመጡ ነው፡፡
ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል እንዳገኘነዉ መረጃ ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ከሶማሌ ላንድ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ እና ደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር ለመፍጠር የሁለትዮሽ ግንኙነት በማድረግ ላይ ትገኛለች።