በተለያዩ የውጭ ሃገራት እስር ቤቶች የሚገኙ 2250 ኢትዮጵያውያን በያዝነው ሳምንት ወደ ትውልድ ሃገራቸው ተመልሰዋል
አርትስ 04/04/2011
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም በመግለጫቸው እንዳመላከቱት ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በየቀኑ 450 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃራቸው እየተመለሱ ነው ይህም እስከ ሳምንቱ መጨረሻ የሚቀጥል ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ባለፉት ጥቂት ወራት በውጭ ሀገር ለሚኖሩ 40 ሺህ አትዮጵያውያን ፓስፖርት መሰጠቱን አሳውቀዋል።
የሌላ ሃገር ዜግነት የወሰዱ ትውልደ ኢትዮጵያውን እንዳሉና ፤ለነዚህ ዜጎችም የኢትዮጵያዊነት መታወቂያ እንደሚሰጣቸው ታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎች በተሰጠው ዕድልም 20 ሺህ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን አስታውቀዋል
አፍሪካውያን ከአሁን በፊት የአፍሪካ መዲና እና የአህጉራዊ ተቋም የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ወደ ሆነችው አዲስ አበባ ለመምጣት የቪዛ አገልግሎቱ ላይ ሲያነሱት የነበረውን ቅሬታም ለአፍሪካ ህብረት አባል ሃገራት መሰጠት በተጀመረው የ ኢ-ቪዛ አገልግሎት ተስተካክሏል ብለዋል አቶ መለስ በመግለጫቸው።
ከሀምሌ ወር 2009 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ ለተለያዩ ሀገራት ዜጎች ቋሚ የመኖሪያ መታወቂያ እየሰጠች መሆኑንም ቃል አቀባዩ ተናረው በዚህም እስካሁን 460 ለሚሆኑ በከፍተኛ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ እና ከኢትዮጵያ ጋር ረጅም ትስስር ያላቸው የውጭ ሀገር ዜጎች ማለትም የአርመኒያ፣ ጣሊያን እና ግሪክ ዜጎች ቋሚ የመኖሪያ መታወቂያ እንደተሰጠ ተናግረዋል፡፡
ለውጭ ሀገር ዜጎቹ የተሰጠው ፈቃድ በየዓመቱ በሚታደሰው የመኖሪያ ፍቃድ ፈንታ የማይታደስ ቋሚ መሆኑን አስረድተዋል።
ለውጭ ሀገር ዜጎች ቋሚ የመኖሪያ ፍቃድ መሰጠቱ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ያብራሩት አቶ መለስ፥ ከእነዚህም መካከል በኢንቨስትመንትና ቱሪዝምን ማስፋፋት አንዱ ነው ብለዋል።
እንዲሁም የኢትዮጵያ የባህል አምባሳደርነታቸውን እንዲያጠናክሩ፣ በገፅታ ግንባታና ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ረገድ ከአሁን በፊት ያላቸውን አስተዋጽኦ ይበልጥ የሚያጠናከር ሲሆን፥ ከሁሉም በላይ ግን ኢትዮጵያ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌትነቷን እና የፓን አፍሪካዊነት አስተሳሰብን ይበልጥ ያጠናክራል ብለዋል፡፡