የቀበሌ ቤቶች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ሊያገኙ ነው
አርትስ 05/04/2011
አዲስ አበባ የመሬት ይዞታ፣ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ለ158 ሺህ የቀበሌ ቤቶች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ልሰጥ ነው አለ
ኤጀንሲው የይዞታ ማረጋገጡን ስራ በአስሩም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ የቀበሌ ቤቶች ከታህሳስ ወር ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ወራት እንደሚያከናውን አስታውቋል፡፡
ስራውን የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ፣ የይዞታ አሰተዳደር የሽግግር ጊዜ ፕሮጀክት ጽ/ቤት እና የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ በቅንጅት እንደሚሰሩት ተነግሯል፡፡
የማረጋገጥ ስራው መዘግየቱ የቀበሌ ቤቶች ከመንግስት ይዞታነት ወደ ግል ይዞታነት እንዲዘዋወሩ ፣ እንዲከፋፈሉ እና ከግል ቤቶች ጋር እንዲቀላቀሉ አድርጓል ተብሏል።
መንግስት ምን ያህል የቀበሌ ቤቶች በማን እጅ እንዳሉ ቆጥሮ በመያዝ በተደራጀ መረጃ ቤቶቹን ለማስተዳደር ብሎም ካርታ ለመስራት እና ለመስጠት እንደሚያስችለው ነው ስራ አስኪያጁ የተናገሩት፡፡
የማረጋገጡ ሂደት ሲጀመር በቀበሌ ቤቶቹ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች በቦታው በመገኘት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡
የማረጋገጥ ሂደቱ ሲያበቃ የይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ይሰጣል ብሏል ከአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ