በቅርቡ በተማሪዎች መካከል በተፈጠረው ረብሻ ሰላሙ ደፍርሶ የነበረው የአምቦ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች የዕርቅ ስነስርዓት ተካሂዶበታል
አርትስ 10/04 /2011
በእርቅ ስነስርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአምቦ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሠ ቀነአ ተማሪዎች የራሳቸውን ደስታ በራሳቸው ማምጣት እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።
በዩኒቨርስቲው የነበረው የሰላም መደፍረስ ሁኔታ ተፈጥሮ ተማሪዎች አብረው ተቀምጠው መነጋገር በመቻላቸው ደስታ የተሰማቸው መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ ይህ ሁኔታ የሰላም አየር እንዲነፍስ መደላድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ “ስንሰማማና አንድ ስንሆን የማንችለው ነገር የለምና ሰላማችንን እንጠብቅ ” የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል ።
ከጥል ምንም ትርፍ አይገኝም ያሉት ዶክተር ታደሠ የአምቦ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ልዩነቶችን አቻችለው በሰላም በመኖር ለሌሎች አርዓያ መሆን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።