ብሩንዲ ጦሯን ከሶማሊያ ላለማስወጣት እያንገራገረች ነው
አርትስ 15/04/2011
የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሀይል ወደ ሶማሊያ የላኩ ሀገራት ቀስ በቀስ ጦራቸውን ወደ ሀገራቸው እንዲመልሱ ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ ብሩንዲ ተቃውሞዋን አሰምታለች፡፡
አፍሪካ ኒዉስ እንደዘገበው ከዩጋንዳ ቀጥላ በአፍሪካ ሁለተኛዋ ብዙ የጦር ሰራዊት አባላትን ወደ ሶማሊያ የላከቸው ብሩንዲ በሚቀጥለው ጥር ወር 1 ሺህ ወታደሮቿን እንድታስወጣ በህብረቱ ተነግሯታል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ሁሉም የሰላም አስከባሪ ጦር ወደ ሞቃዲሾ የላኩ ሀገራት ጦራቸውን በተወሰነ ቁጥር እንዲቀንሱ የወሰንኩት ሶማሊያዊያን ራሳቸውን ለመቻል የሚያደርጉት ጥረት እየተሳካ ስለሆነ ነው ብሏል፡፡
የብሩንዲ ከፍተኛ ባለስልጣናት ግን የህብረቱን ውሳኔ በጥርጣሬ ዓይን እንደሚመለከቱት ነው የሚናገሩት፡፡
ይሄ ሀሳብ ከአውሮፓ ህብረት የመነጨ መሆኑን በሚገባ አናውቃለን፤ ምክንያቱም ብሩንዲን ለመጉዳት ታስቦ የተደረገ ነው ብለዋል ባለስልጣናቱ፡፡
ቡጁምቡራ ሀሳቡን የተቃወመችው ለላከችው የሰላም አስከባሪ ጦር የአፍሪካ ህብረት በየወሩ የሚከፍላት 6 ሚሊዮን ዶላር እንዳይቀንስባት በመስጋቷ ነው፡፡
ብሩንዲ በሰብዓዊ በመብት አያያዟ ከአፍሪካ ህብረትና በዓለም አቀፍ ተቋማት ብርቱ ወቀሳ የሚደርስባት ሀገር ስትሆን በማእቀብ ሳቢያ ያለባትን ኢኮኖሚያዊ ጫና ከሰላም ማስከበር በምታገኘው ከፍያ ለመደጎም ትፈልጋለች ተብሏል፡፡