በሙስና የተወሰዱ ንብረቶችን ለማስመለስ የህግ ክፍተት አለ ተባለ
አርትስ 17/04/11
ይህንን ያለው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ነው።
የኦሮሚያ ክልል የጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበበ ከበደ እንዳሉት በክልሉ ህገ ወጥ የመሬት ወረራ ፣ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ስልጣንን ያላግባብ መጠቀም እና ሌሎች የተደራጀ ሌብነቶች እየተፈጸሙ ነው።የተጭበረበረ ሰነድ በመጠቀም እና በኢንቨስትመንት ስም የመንግስት ገቢን እስከ ማስቀረት የሚደርስ ወንጀልም አለ።
የወንጀል አይነቱ በተደራጁ አካላት መፈጸም ደግሞ ስራውን ውስብስብ አድርጎታል ነው ያሉት ኮሚሽነሩ።
በእርዳታ እና ብድር መልኩ ከተለያዩ የውጭ ተቋማት የሚገኙ የበጀት አይነቶች በከፍተኛ ደረጃ ለዚህ ችግር ተጋላጭ እንደሆኑ ተደርሶበታል ብለዋል ።
ይህንን ወንጀል ለመከላከል ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረው በማስረጃ ተደግፈው የቀረቡትም በህጋዊ መንገድ እንዲጠየቁ እየተደረገ ነው ብለዋል።
እስካሁን ከ16 ቶን በላይ ብረት እና ያላግባብ የተያዘ 6 ሺህ ሄክታር መሬት ለመንግስት ገቢ መደረጉን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
ያም ሆኖ በዝርፊያ መልኩ የተወሰደውን ሀብት ለማስመለስ የህግ ክፍተቶች አሉ ያሉት ኮሚሽነር አበበ ይህ ችግርአም ለወደፊቱ መታየት ለበት ብለዋል።
ኮሚሽኑ በአሁኑ ጊዜ በክልሉ በሚገኙት ስምንት ቅርንጫፎች የተደራጀ ፀረ ሙስና ትግል እያካሄደ መሆኑንም ተናግረዋል ፋና እንደዘገበው።