በሱዳን የተነሳውን ተቃውሞ የሃገሪቱ ጋዜጠኞችም ተቀላቅለውታል
አርትስ ታህሳስ 19 2011
በሱዳን የዳቦ ዋጋ ጭማሪን አስታክሎ የተነሳውን ከባድ ሃገራዊ ተቃውሞ ሱዳናውያን ጋዜጠኞችም ተቀላቅለውታል እየተባለ ነው።
የሱዳን ጋዜጠኞች ጥምረት የሰዎችን ህይወት ወደመቅጠፍ የተሸጋገረውን ተቃውሞ ትናንት መቀላቀላቸውን አስታውቀዋል፡፡
መንግስት በሰልፈኞች ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ በመቃወም ጋዜጠኞቹ ከታህሳስ 27 ቀን ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚዘልቅ አድማ ጀምረናል ብለዋል። የጋዜጠኞቹ ጥምረት አድማውን የተቀላቀለው በሃገሪቱ የተነፈግነውን በነፃነት መናገር መብት ለማስከበር ነው ብለዋል።
የሱዳን ጋዜጠኞች ከባለስልጣናት ጥቃት እንደሚደርስባቸው በመግለጽ በተደጋጋሚ አቤቱታቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል።
የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አሁን በሃገሪቱ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እንዳይስፋፋ ጋዜጦቹን በማስገደድ ለማሳመን እየተጠቀመባቸው ነው ተብሏል፡
አክቲቪስቶችና ተቃዋሚ ቡድኖች በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ሱዳናውያን ተቃውሞውን ለማስፋት ወደ ጎዳና እንዲወጡ ጥሪ በማስተላለፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ የመንግስት ተቃዋሚ ቡድኖችም አድማና አመጹን ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም እንዲቀላቀሉትና ተቃውሞውን እንዲያጠናክሩ ጥሪያቸውን በማስተላለፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
የሱዳን ኮሚኒስት ፓርቲ በበኩሉ ይህንን ስርዓት ለመገርሰስ የምናደርገው ጥረት እስክናሳካ ድረስ የሱዳን ህዝቦች ተቃውሞውን አጠናክሮ እንዲቀጥል እናሳስባለን ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡
የፕሬዚዳንት ኦማር አል- በሽር መንግስት ረቡዕ በየሀገሪቱ ኢኮኖሚ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን በመቃወም በወጡ ሰልፈኞችን ፖሊስ ለመበተን በሚያደርገው ጥረት የሰዎች ህይወት ጠፍቷል። የመንግስት ባለስልጣናት በተፈጠረው ግጭት የስምንት ተቃዋሚዎች ህይወት ማለፉን ቢናገርም አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሟቾቹን ቁጥር ወደ 37 ከፍ አድርጎታል፡፡ዜናውን ከሮይተርስ እና አፍሪካ ኒውስ አግኝተነዋል።