ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ በሰንዳፋ ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ምንም አይነት ቆሻሻ አይጣልም አሉ
ኢ/ር ታከለ ኡማ ከሳይንስ እና ኢኖቬሺን ሚንስትሩ ጌታሁን መኩሪያ እና ከከተማዋ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ጋር በጋራ በመሆን የሰንዳፋ ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀክት አከባቢ ከሚገኙ ነዋሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ባለበት የኦፕሬሽናል ችግር ምክንያት ለከፍተኛ ጉዳት እየተጋለጡ ያሉትን የአካባቢውን ነዋሪዎች ከቆሻሻው የሚለቀቀው ፍሳሽ ማሳቸውን ሙሉ ለሙሉ ማውደሙን እና ወደ መኖሪያ ቤታቸው ጭምር በመግባት ለከፍተኛ የጤና ችግር እየተጋለጡ እንደሚገኙ አንስተዋል።ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ፕሮጀክቱ ለ 8 ወር ብቻ አገልግሎት ከሰጠ በኋላ ከአካባቢው ነዋሪዎች በደረሰበት ተቃውሞ ምክንያት ከሁለት አመት በፊት አገልግሎት ማቆሙ ይታወሳል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የስራኃላፊዎች ከህብረተሰቡ ለተነሱ ቅሬታዎች በሰጡት ምላሽ የከተማ አስተዳደሩ በፕሮጀክቱ ምክንያት እርሻቸው ላይ ጉዳት ለደረሰባቸው አርሶ አደሮች በቂ ካሳ እንደሚከፈል እና እስከ አሁን በአከባቢው የተከማቸውንም ቆሻሻ በሳይንሳዊ መንገድ ችግሮቹን ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዚህ በኃላ የትኛውንም አይነት ቆሻሻ በአከባቢው እንደማይጥልም ለአርሶአደሮቹ ቃል ገብተዋል፡፡ የከንቲባ ፅ/ቤት እንዳስታወቀው፡፡