ሩዋንዳ ድንበሯን በመዝጋቷ በሺዎች የሚቆሩ ኮንጓዊያን በምርጫ አይሳተፉም
አርትስ 21/04/2011
በምስራቃዊ ኮንጎ ያለው ሰላም በመደፍረሱ ደህንነታቸው ስጋት ላይ የወደቀ ቁጥራቸው ከ40 ሺህ ያላነሰ የዲሞከራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ ተወላጆች ተሰደው በጎረቤት ሩዋንዳ ይኖራሉ፡፡እነዚህ ጎንጓዊያን በሀገራቸው የተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ እቅድ የነበራቸው ቢሆንም ሩዋንዳ መተላለፊያ ድንበሯን በመዝጋቷ ውጥናቸው ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡
አፍሪካ ኒውስ እንደዘገበው የፖል ካጋሜ መንግስት ድንበሩን አጥብቆ የዘጋው ወጭ ገቢ በበዛ ቁጥር ሀገሬ የፀጥታ ችግር ይገጥማታል ብሎ በመስጋቱ ነው፡፡
በሰላም እጦት ምክንያት ወደ ሩዋንዳ ከተሰደዱት መካከል ዳንኤል ሚቾምቦሮ እና ሲፋ ካባንዳ የሀገራቸው መንግስት ከሩዋንዳ መንግስት ጋር በመነጋገር መሪዎቻችንን የመለምረጥ መብታችንን ሊያመቻችልን ይገባ ነበር ይላሉ፡፡ሚቾምቦሮ፣ መንግስት ቀድሞ ቢዘጋጅበት ኖሮ ወይ ወደ ሀገራችን ተጉዘን አልያም ባለንበት ሆነን ድምጸችንን እንድንሰጥ ሁኔታዎችን ያመቻችልን ነበር ፤ ዳሩ ግን እኛን የፈለገን አይመስልም በማለት የካቢላን አስተዳደር ወቀቅሷል፡፡
ለምሳሌ እኔና ባለቤቴ እንዲሁም እድሜያቸው ለመምረጥ የደረሰ ስድስት ልጆቻችን እድሉን ባለመጠቀማችን በኛ ቤት ውስጥ ብቻ ስምንት ድምፅ ባክኗል ያለችው ደግሞ ሌላዋ ስደተኛ ሲፋ ካባንዳ ነች፡፡
በአዲሱ ዓመት ዋዜማ በተካሄደው የዲሞክራቲክ ኮንጎ ምርጫ በቤኒ እና ቡቴምቤ አካባቢዎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንዲሁም በዩምቢ ክልል 60 ሺህ መራጮች አይሳተፉበትም፡፡
በነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች በመጭው መጋቢት ወር ምርጫ እንዲያካሂዱ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል፡፡
ሀገሪቱን ለ17 ዓመታት ያስተዳደሩት ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ በማይሳተፉበት ቢዚህ ምርጫ ከ46 ሚሊዮን በላይ ኮንጓዊያን ድምፃቸውን ለመስጠት ተመዝግበዋል ነው የተባለው፡፡