አስተዳደሩ ከ134 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ አቅዷል
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እንዳሉት ቤቶቹ የሚተላለፉት በሚቀጥሉት 8 ወራት ውስጥ ነው።
ምክትል ከንቲባው ይህንን የገለጹት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 6ኛ የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የ2011 በጀት ዓመት የ6 ወር እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ነው።
ምክትል ከንቲባው በሪፖርታቸው አስተዳደሩ ያዋቀረው አዲስ ካቢኔ ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ ስራዎች አከናውኗል ነው ያሉት።
ከነዚህም መካከል በ6 ወራት ብቻ ለ648 ዜጎች የመስሪያ ቦታ በመተላለፉ አስተዳደሩ ከ134 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ አቅዷልውና በ116 ወረዳዎች የመካከለኛ እና አነስተኛ ስፖርት ማዘውተሪያ ግንባታዎች መጀመራቸውን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።
ምክትል ከንቲባው በሪፖርታቸው ካነሷቸው ዋና ጉዳዮች ውስጥ የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍም በከተማው የተከናወኑ ተግባራት ላይ ያተኮረ ሲሆን በዚህም በ20/80 እና የኪራይ ቤቶች ፕሮግራም 95 ሺህ ቤቶች እንዲሁም በ40/60 ደግሞ 38 ሺህ 200 ቤቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ በተያዘው የ2011 በጀት ዓመት 134 ሺህ 72 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ እየሰራ መሆኑንም ምክትል ከንቲባ ታከለ በሪፖርታቸው አስታውቀዋል።
እንደ ምክትል ከንቲባው ገለጻ ባለፉት 6 ወራት ከህብረተሰቡ በደረሱ ጥቆማዎች 1 ሺህ 666 በህገ ወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ የቀበሌ ቤቶች እና 2 ሺህ 436 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተለይተው ለትክክለኛ ተጠቃሚዎች እንዲተላለፉ መደረጉን ኤፍቢሲ ዘግቧል።