በኢንቨስትመንት ስም ከቀረጥ ነፃ ወደኢትዮጵያ የሚገቡ የብረት ምርቶች ለህገ ወጥ ስራ እየዋሉ በመሆኑ መንግስት ማግኘት የሚገባውን ከፍተኛ ገንዘብ እያሳጣው መሆኑን የጉሙሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።
የብረት ምርት ፍላጎት በከፍተኛ መጠን ባደገባት ኢትዮጵያ መንግስት ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት በሆቴሎች እና መሰል ዘርፎች ላይ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ብረት ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ ፈቅዷል።
ነገር ግን ይህን የማበረታቻ እድል ባልተገባ ሁኔታ እየተጠቀሙ የሚገኙ ግለሰቦች መንግስትን ገንዘብ በማሳጣት ሀገሪቱን በከፍተኛ ደረጃ ሲጎዷት ቆይተዋል።
የጉሙሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሙለታ በየነ ከኤፍቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት በርካታ ድርጅቶች በሆቴል ዘርፍ ለመሰማራት ፍቃድ ቢያወጡም ማበረታቻውን ከተጠቀሙ በኋላ ግንባታውን ማቋረጣቸውን ተናግረዋል።
ለአንድ ህንፃ ምን ያህል የብረት መጠን እንደሚያስፈልገው አለመታወቁ ይህንን ማጭበርበር ለመከላከል አስቸጋሪ ሆኗል ብለዋል።
ጉሙሩክ ኮሚሽን ያቋቋመው የምርመራ ቡድን ኦዲት አድርጎ ሲጨርስ እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምርም ተናግረዋል፡፡