Uncategorized

መከላከያ ሰራዊት ጎሳን መሰረት ያደረገ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች በፍጥነት በመግባት ኅብረተሰቡን እያረጋጋሁ ነው አለ

መከላከያ ሰራዊት ጎሳን መሰረት ያደረገ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች በፍጥነት በመግባት ኅብረተሰቡን እያረጋጋሁ ነው አለ።

መከላከያ ሚኒስቴር ይህንን የተናገረው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 17ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የሚኒስቴሩን የ6 ወር የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት ነው።

የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ እንዳሉት፤ የመከላከያ ሰራዊትን ብቁና ገለልተኛ ለማድረግ ባለፉት 6 ወራት የአሰራርና የአደረጃጀት ለውጦች ተደርገዋል።

ከነዚህም መካከል የመከላከያ ሰራዊት አዋጁን ማሻሻል፣ የባህር ሃይልን ማደራጀት፣ ሰራዊቱን በህገ መንግስቱ ከተሰጠው ተልዕኮ አንፃር ማዋቀር ይገኙበታል።

በዚህም ከኅብረተሰቡና ከአካባቢው የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር በአንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ግጭት ማረጋጋት ተችሏል ብለዋል።

በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ የደቡብ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ክልል እና በሌሎች አካባቢዎች የተከሰቱትን ግጭቶች በማርገብም አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን መደረጉን ተናግረዋል።

የጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ በበኩላቸው “ሰራዊቱ በህብረብሄራዊ አደረጃጀቱ በየትኛውም አካባቢ የሚከሰቱ ግጭቶችን ማስቆም ይችላል” ብለዋል።

በዚህም ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ፈጥኖ በመግባት የአካባቢው ማህበረሰብ ሰላም እንዲመለስ እያደረገ ነው ብለዋል።

ምክር ቤቱ በበኩሉ መከላከያ ሰራዊቱ ውስጣዊ አደረጃጀቱን በሚገባ በመፈተሽ የሰላም ዘብና የሀገር ኩራት መሆኑን በዘላቂነት ማረጋገጥ እንደሚገባው አሳስቧል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

 

Show More

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button
Close
Close
Close Bitnami banner
Bitnami