በኮፓ ዴል ሬይ ባርሴሎና ሽንፈት ገጥሞታል
በስፔን ኮፓ ዴል ሬይ የመጨረሻ 16ቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ባርሴሎና ከሜዳው ውጭ በሌቫንቴ የ2 ለ 1 ሽንፈት አስተናግዶ ተመልሷል፡፡
ኢሪክ ካባኮ እና ቦርያ ማዮራል ለሌቫንቴ በመጀመሪያው አጋማሽ 20 ደቂቃ ውስጥ ያስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች አሸናፊ እንዲሆን አግዘዋል፡፡
ብራዚላዊው አማካይ ፊልፔ ኮቲንሆ በ85ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምት ግብ የቡድኑን ከባዶ መሸነፍ ያደነች ጎል ከመረብ አገናኝቷል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በላሊጋው ከሶስት ሳምንት በፊት ተገናኝተው የሊዮኔል ሜሲን ሶስት ግቦች ጨምሮ ባርሳ 5 ለ 0 መርታቱ ይታወሳል፡፡
የመልስ ጨዋታው በሚቀጥለው ሳምንት በኑካምፕ ይደረጋል፡፡
በሌሎች ጨዋታዎች ሲቪያ አትሌቲክ ቢልባዎን 3 ለ 1 ሲረታ፤ ሪያል ቤቲስ ከ ሪያል ሶሴዳድ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡