ሜጀር ጄኔራል ክንፈን ጨምሮ ስምንት ተከሳሾች ከ319 ሚሊየን ብር በላይ በማባከን ክስ ተመሰረተባቸው
የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር የነበሩትን ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ በስምንት ግለሰቦች ላይ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ከ319 ሚሊየን ብር በላይ በመንግስት ላይ ጉዳት አድርሰዋል ሲል ክስ መስርቷል፡፡
ስምንቱ ተከሳሾች ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም ወንጀል ሰባት ክሶች ቀርቦባቸዋል፡፡
በክስ ሰነዱ ላይ እንደተመላከተው ክሱ የተፈፀመው በብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የአዳማ እርሻ መሳሪያዎች ኢንዱስትሪ አገልግሎት የሚውሉ ትራክተር እና የትራክተር ተሳቢዎች ግዥ ያለግልፅ ጨረታ፣ ያለግዥ ፍላጎት እና ለሁሉም አቅራቢዎች እኩል እድል ባልሰጠ መልኩ ተካሂዷል በሚል ነው፡፡
በዚህም መንግስት ከገበያ ውድድር ሊያገኝ የሚችለውን የጥራት፣ የዋጋና የአቅርቦት ጥቅም ጎድተዋል ያለው ከሳሽ አቃቢ ህግ ይህንም ለማስረዳት የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን ዐቃቢ ህግ በክስ ዝርዝሩ አያይዞ አቅርቧል።
ተከሳሾች የክስ መዝገቡ ችሎቱ ላይ ስለደረሳቸው በጠበቆቻቸው አማካኝነት መቃወሚያቸውን ለማቅረብ ተለዋጭ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቀዋል፡፡
አቃቢ ህግም በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያቀረባቸው የሰነድ ማስረጃዎች በአማርኛ ተተርጉመው በ10 ቀናት ውስጥ ለፍርድ ቤቱ እንዲቀርቡም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱም ለጥር 17 ቀን 2011 አመተ ምህረት ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ሪፖርተር አስነብቧል፡፡