Legal

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በከተማዋ የሚፈጸሙ የጦር መሳሪያና ህገወጥ ገንዘብ ዝውውር ላይ ባካሄደው አሰሳ ከፍተኛ ውጤት ማግኘቱን አስታወቀ

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በከተማዋ የሚፈጸሙ የጦር መሳሪያና ህገወጥ ገንዘብ ዝውውር ላይ ባካሄደው አሰሳ ከፍተኛ ውጤት ማግኘቱን አስታወቀ።

 ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ2ሺ በላይ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች እና ከ50 ሺ በላይ ጥይቶች ተይዘዋል ብሏል። ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኢትዮጵያ እና የውጭ ሃገራት ገንዘቦች መያዙንም አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኢንዶክትሪኔሽንና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው የከተማዋ ፖሊስ የጦር መሳሪያዎቹን የያዘው ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ነው።

በዚህ የተቀናጀ ስራ ከሀምሌ 1ቀን 2010 እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ባለው የስድስት ወር ጊዜ ብቻ 2 ሺህ 383 ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎች መያዛቸውን የጠቀሰው መግለጫው ከተያዙት የጦር መሳሪያዎች መካከል ሁለት የእጅ ቦንብና አንድ መትረየስ ይገኝበታል ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪ 56 ሺህ 615 ጥይት መያዙን አስታውቋል ። እንደመግለጫው ባለፉት ስድስት ወራት የህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል በተካሄደው አሰሳ ከ68 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ የተያዘ ሲሆን 88 ሺህ 151 የአሜሪካ ዶላር ፣ 9 ሺህ 480 ዮሮ ፣ እንዲሁም 12 ሺህ 620 ፓውንድ እና በርከታ የሌሎች ሀገራት ገንዘቦች መያዛቸውን ኮሚሽኑ ከላከው ዘገባ መረዳት ተችሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም 163 ሺህ 600 ሃሰተኛ ብር እንዲሁም 3800 ሃሰተኛ የአሜሪካ ዶላር መያዙንም መግለጫው አመልክቷል። ህገወጥ የገንዘብ አዘዋዋሪዎች ወንጀላቸውን ለመከለል በማሰብ ለፖሊስ አባላት ከሁለት ሚለዮን ብር በላይ መደለያ ሲሰጡ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውንም የፖሊስ ኮሚሽኑ በመግለጫው  አብራርቷል።

 

Show More

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button
Close
Close
Close Bitnami banner
Bitnami