የአልሸባብ ታጣቂዎች ናይሮቢ ወስጥ ባደረሱት ጥቃት 15 ሰዎች ተገደሉ
ከሟቾቹ መካከል የአሜሪካ እና የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች እንደሚገኙበት የሁለቱ ሀገራት መንግስታት ይፋ አድርገዋል፡፡
የኬንያ ፖሊስ አዛዥ ጆሴፍ ቦይኔት እንዳሉት ታጣቂዎቹ በአንድ ዘመናዊ ሆቴል ላይ ፍንዳታ በማድረስ እና ተኩስ በመክፈት ነው ጥቃቱን የጀመሩት፡፡
ዘ ኢንዲፔንደንት እንደዘገበው አልሸባብ ለጥቃቱ ሐላፊነት ከመውሰዱም በላይ ደጋፊዎቹ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የደስታ መልዕክት ሲለዋወጡ ተስተውለዋል።
የሟቾቹ ቁጥር 15 ነው ቢባልም አልሻባብ በመግለጫው ቁጥሩን ወደ 48 ከፍ አድርጎታል።
ኬንያ እንደዚህ ዓይነት የአጥፍቶ ጠፊዎች ጥቃት ሲደርስባት ያሁኑ የመጀመርያ አይደለም።
የአልሻባብ ታጣቂዎች ከዓመታት በፊት ዌስትጌት በተባለ የገበያ አዳራሽ በከፈቱት ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኬንያውያንን መግደላቸውና ማቁሰላቸው ይታወሳል።
እንደዚሁም ጋሪሳ በተባለው ከተማ አንድ ኮሌጅ ላይ በከፈቱት ጥቃት 148 ተማሪዎችንና የኮሌጁን አስተዳደር ሰራተኞችን መግደላቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
የአሁኑን ጥቃት ከነዚህ ጥቃቶች ጋር የሚያገናኘው ከዌስትጌቱ ጥቃት ጋር እጃቸው አለበት የተባሉ ሰዎች ጉዳይ በፍርድ ቤት እየታየ ያለበት ወቅት ላይ የተፈጸመ መሆኑ ነው ተብሏል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የታክሲ አገልግሎት በመስጠት የሚታወቀው ኡበር የኬንያው ቅርንጫፍ በናይሮቢ ለሚገኙና ለተጎዱት ሰዎች ደም ለመለገስ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን ነፃ የደርሶ መልስ ትራንስፖርት እየሰጠ ይገኛል።