በኮፓ ዴል ሬይ ባርሳ አሸንፏል
የካታላኑ ባርሴሎና ትናንት ምሽት በኑካፕ ስታዲየም የኮፓ ዴል ሬይ የመልስ ጨዋታውን ከሌቫንቴ ጋር አከናውኗል፡፡
በጨዋታው ወጣቱ ኦስማን ዴምቤሌ በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ባስቆጠራቸው ሁለት እና አምበሉ ሊዮኔል ሜሲ ባከላት ተጨማሪ ጎል የቫሌንሲያውን ቡድን 3 ለ 0 አሸንፏል፡፡
የሜሲ ያስቆጠራት ግብ በአምስት ጨዋታዎች ሰባተኛ ግቡ ሆና ተመዝግባለታለች፡፡
ባርሴሎና ድል ማድረጉን ተከትሎ በ4 ለ 2 የድምር ውጤት ወደ ሩብ ፍፃሜው ተሻግሯል፡፡ ነገር ግን ቡድኑ በውድድሩ የመጀመሪያ ጨዋታ ተገቢ ያልሆነ ተጫዋች አሰልፏል፤ በማለት ሌቫንቴዎች ክስ በማሰመዝገባቸው ከውድድሩ ውጭ ሊሆን እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል፡፡
በኮፓ ዴል ሬይ የመጀመሪያ ጨዋታ ቫሌንሲያ ላይ ሌቫንቴ 2 ለ 1 ባሸነፈበት ግጥሚያ፤ ዩአን ብራንዳሪዝ የተሰኘ የተከላካይ መስመር ተሰላፊ ተጫዋች በሴጉንዳ ቢ ዲቪዥን ውድድር ለባርሴሎና ቢ ቡድን ሲጫወት አምስት ቢጫ ካርዶችን ተመልክቶ እያለ ለዋናው ቡድን ተሰልፎ አገልግሎት ሰጥቷል ሲሉ ሌቫንቴዎች ለስፔን ፌዴሬሽን አቤቱታ አሰምተዋል፡፡
ባርሴሎናዎች ግን በህዳር ወር አዲስ የወጣው ህግ በኮፓ ዴል ሬይ ተግባራዊ አይሆንም፤ እናም ህጋዊ ነን እያሉ ነው፡፡
በኮፓ ዴል ሬይ ከዚህ ቀደም በ2015 ዴኒስ ቼሪሸቭን ያለአግባብ ያሰለፈው ሪያል ማድሪድ ከውድድር መሰረዙ ይታወሳል፡፡
በሌሎች ጨዋታዎች ሪያል ሶሴዳድ ከ ሪያል ቤቲስ 2 ለ 2 አቻ ቢለያዩም፤ በአጠቃላይ ውጤት ቤቲስ ከሜዳው ውጭ ጎል ባስቆጠረ በሚለው ህግ ወደ ሩሲያልፉ፤ ሌላኛው የካታላን ቡድን ኢስፓኞል ቪያሪያልን 3 ለ 1 በድምር ውጤት ደግሞ 5 ለ 3 ወደ ቀጣዩ ዙር ተቀላቅሏል፡፡
ሪያል ማድሪድ፣ ሲቪያ፣ ቫሌንሲያ፣ ጅሮና፣ ሄታፌ፣ ኢስፓኞል እና ሪያል ቤቲስ ወደ ሩብ ፍፃሜው የተቀላቀሉ ቡድኖች ናቸው፡፡