የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ውዝፍ ክፍያ ማስከፈል ጀምሬያለሁ አለ
የአገልግሎት ክፍያ በወቅቱ ካልከፈሉ ደንበኞች እስካሁን 340 ሚሊየን ብር መሰብሰቡንም ተናግሯል
የአገልግሎቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ እንደተናገሩት አገልግሎቱ ከዚህ በፊት ያልከተፈሉ ውዝፍ ክፍያዎችን ተከታትሎ እየሰበሰበ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ከሰበሰበው በተጨማሪ ከ350 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆን ከደንበኞች ያልተሰበሰበ ውዝፍ ክፍያ አለኝ ይላል አገልግሎቱ።
የማስከፈሉ ስራ መቀጠሉን የተናገሩት ዋና ስራ አስፈጻሚው የአገልግሎት ክፍያቸውን በወቅቱ በማይከፍሉ ደንበኞቹ ላይ እርምጃ መውሰድ ጀምሯል ብለዋል።
እንደዋና ስራ አስፈፃሚው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በዚህ ዓመት ከ9 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት እየሰራ ነው።
ተቋሙ ዓመታዊ ወጭው እና የሚያገኘው ገቢ ፈፅሞ አይገናኝም የተባለ ሲሆን በያዝነው ዓመት ለሚከወኑ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ብቻ 35 ቢሊየን ብር ያስፈልጋል ነው ያሉት።