የቱኒዚያ መንግስት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰራተኞቹ ጋር ተኳርፏል
በቱኒዚያ በተፅእኖ ፈጣሪነቱ የሚታወቀው ጀኔራል ሌበር ዩኒየን በመላ ሀገሪቱ መንግስትን ለመቃወም ባደረገው ጥሪ የአውቶቡስ፣ የባቡር እና የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጧል፡፡
በሀገሪቱ መንግስት የሚተዳደረው ቱኒዚያ ኤየር የተባለው አየር መንገድ ነገሩ ሳይለይለት በረራ አላደርግም ብሎ ደንበኞቹ የጉዞ ፕሮግራማቸውን ለሌላ ቀን እንዲያዛውሩ በመንገር አሰናብቷቸዋል፡፡
ትምህርት ቤቶች ፣ሆስፒታሎች እና ሌሎች የመንግስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማትም በአመፁ ሳቢያ ተዘግተው ውለዋል ነው የተባለው፡፡
የሰራተኛ ማህበሩ የተቃውሞ ሰልፉን የጠራው መንግስት ለ670 ሺህ ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ ባለመመለሱ ነው፡፡
ሮይተርስ እንደዘገበው የአሁኑ አመፅ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2013 አንድ የተቃዋሚ ፖለቲከኛ መገደላቸውን ተከትሎ ከተደረገው ሰልፍ ወዲህ በትልቅነቱ ተወዳዳሪ የለውም፡፡
የቱኒዚያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዩሱፍ ቻህድ አመፁ ብዙ ዋጋ ቢያስከፍለንም ሀገራችን የገባችበት የኢኮኖሚ ቀውስ በተጠየቀው ልክ ደሞዝ ለመጨመር አያስችላትም ነው ያሉት፡፡
የሰራተኛ ማህበሩ የጠየቀው የደሞዝ ጭማሪ መንግስትን 850 ሚሊዮን ዶላር የሚያስወጣው ሲሆን ለመክፈል የተስማማው ግን ከግማሽ በታች ነው፡፡
ቱኒዚያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ በፈረንረጆቹ 2016 ለተፈቀደላት የ2.8 ቢሊዮን ዶላር ብድር የተቀመጠላትን ቅድመ ሁኔታ ለማሟላት እየታገለች ትገኛለች፡፡