ለጥቁር ገበያ ለሽያጭ ሊቀርብ የነበረ ነዳጅ እና ግምቱ ከ1ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ልዩ ልዩ ቁሳቁስ መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተናገረ፡፡
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው በተለምዶ 7ኛ ሸንኮራ በረንዳ ተብሎ ከሚጠራ አካባቢ ከሚገኘው «ትዕግስት ብሩክ ቶታል ማደያ» ውስጥ ጥር 12 ቀን 2011 ዓ/ም የተቋሙ ሰራተኞች ከህገ-ወጦች ጋር በመተባበር በ44 ጀሪካን 995 ሊትር ቤንዚን ከማደያው በመቅዳት ላይ እንዳሉ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከህዝብ በደረሰው ጥቆማ መሰረት የተቀዳውን ቤንዚን እና ሌላ ሊቀዳበት የነበረ 44 ባዶ ጀሪካን እንዲሁም የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 አ/አ 29642 አይሱዙ ተሽከርካሪን ከአምስት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ፖሊስ ተናግሯል፡፡
የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዲቪዚዮን ኃላፊ ኮማንደር ጌታነህ በቀለ የማደያው ሰራተኞች ቤንዚን በጥቁር ገበያ ከሚሸጡ ህገ-ወጦች ጋር በመተባበር ድርጊቱን መፈፀማቸውን ፖሊስ በምርመራው ማረጋገጡን ተናግረዋል፡፡
በህገ-ወጥ ተግባሩ ላይ ተሳትፎ ያደረጉ አምስት ግለሰቦች ምርመራ እየተጠራባቸው እንደሚገኝ ኮማንደር ጌታነህ አስረድተዋል፡፡
በቁጥጥር ስር የዋለው ቤንዚን ከ11 ሺ ብር በላይ ዋጋ እንደሚያወጣ ኃላፊው ተናግረው በልዩ ልዩ ጊዜያት ግምቱ 38 ሺ ብር በላይ የሚያወጣ 112 ጀሪካን ቤንዚን ተይዞ ምርመራው ተጣርቶ የምርመራ መዝገቡ ለዓቃቤ ህግ መላኩን ከኮማንደሩ ገለፃ መረዳት ተችሏል፡፡
ምንጭ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን