የ55 ደረጃዎች ልዩነት ያላቸው ክለቦች ዛሬ ምሽት በካራባዎ ዋንጫ ይገናኛሉ
የእንግሊዝ ፉትቦል ሊግ ካፕ (ካራባዎ ዋንጫ) አንድ የግማሽ ፍፃሜ፤ የመልስ ጨዋታ ዛሬ ምሽት 4፡ 45 ይከናወናል፡፡
በዚህም በምሽቱ ማንችስተር ሲቲ በሊግ አንድ እየተፎካከረ ወደሚገኘው ክለብ በርተን አልቢዮን አቅንቶ በፒረሊ ስታዲየም የመርሀግብር ማሟያ ጨዋታ ያከናውናል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ግጥሚያ ኢቲሃድ ላይ ተገናኝተው፤ ሲቲ 9 ለ 0 መርታቱ ይታወሳል፡፡ በርተን ለፍፃሜ ዋንጫ ለማለፍ በ10 የግብ ልዩነት ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡
ሲቲ በፕሪምየር ሊጉ ለዋንጫ የሚፎካከር ሲሆን በርተን ደግሞ በእንግሊዝ የእግር ኳስ እርከን ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ፤ ከዚያም ባለፈ በዚህም እርከን 13ኛ ደረጃ ይገኛል፡፡
ለዚህም ይመስላል የበርተን አሰልጣኝ ኒጀል ክላፍ በመልሱ ጨዋታ አንድ ተጫዋች ግብ ቢያስቆጥር ክብር ነው ያሉት፡፡
በሊግ ካፕ ዋንጫ ታሪክ በድምር ውጤት ከፍተኛው የግብ መጠን የተመዘገበው 11 ጎሎች ሲሆን ሲቲ ይህንን ክብረወሰን ለመሻገር በምሽቱ ሶስት ግቦችን ማስቆጠር ይጠበቅበታል፡፡
በርተን በጨዋታው ውጤቱን ለመቀልበስ ሙከራ ያደርጋል ተብሎ የማይጠበቅ ሲሆን በድጋሜ በሰፋ የግብ ልዩነት ተሸንፎ ላለማስደፈር መረቡ ላይ ትኩረት ያደርጋል፤ ቢሆንም እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ በርንሊን፣ አስቶን ቪላን፣ ኖቲንግሃም ፎረስትን እና ሚድልስብራን ድል እያደረገ ነው፡፡
በፔፕ ጓርዲዮላ ቡድን በኩል ለሁለት ወራት ያህል ጉዳት ላይ የነበረው ቤንጃሚን ሜንዲ ተመልሶ የመሰለፍ ዕድል እንደሚሰጠው ተጠቁሟል፤ ኬቨን ዴ ብሯይኔም ቢሆን ይሰለፋል ተብሏል፡፡ ጓርዲዮላ በቀሪዎቹ የሜዳ ክፍሎች፤ የመሰለፍ ዕድል ላልተሰጣቸው ወጣት ተጫዋቾች ዕድል ሊሰጣቸው እንደሚችል ተነግሯል፡፡