በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙ አምባሳደሮች በሃገሪቱ የሚካሄደውን የለውጥ ሂደት አእንደሚደግፉ አስታወቁ።
በኢትዮጵያ የተጀመረውን የፖለቲካና ምጣኔ ኃብታዊ ለውጥ እንደሚደግፉ በአገሪቱ አዲስ የተሾሙ የስምንት አገራት አምባሳደሮች ገለፁ።
አምባሳደሮቹ ይህንን የተናገሩት በብሄራዊ ቤተ መንግስት ቀርበው ለፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሹመት ደብዳቤያቸውን ባቀረቡበት ወቅት ነው።
አዲስ ተሿሚዎቹ የካናዳ፣የቱርክ፣ የሴራሊዮን፣ የኢኳቶሪያል ጊኒ፣ የስሎቫኪያ ሪፐብሊክ፣ የሰርቢያ እንዲሁም ተቀማጭነታቸው በካይሮ እና ናይሮቢ ያደረጉት የማልታ እና የኮሎምቢያ አምባሳደሮች ናቸው።
አምባሳደሮቹ ከፕሬዚዳንቷ ጋር በነበራቸው ቆይታ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሁለንተናዊ የለውጥ እርምጃ አድንቀዋል።
አገሪቱ በተለይ ከኤርትራ ጋር የመሰረተችውን ሰላም እና በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን በመጫወት ላይ ያለችውን ሚና እንደሚያደንቁም ገልጸዋል።
በቆይታቸውም ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የትብብር ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። ፕሬዝዳንት ሰህለወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው ሁሉን ዓቀፍ ለውጥ ለአምባሳደሮቹ አብራርተዋል።
እንደኢዜአ ዘገባ ኢትዮጵያ ከአገሮቹ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብሮች አጠናክራ እንደምትቀጥል ለአምባሳደሮቹ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ አምባሳደሮቹ በኢትዮጵያ ቆይታቸው የመንግስት ድጋፍ እንደማይለያቸው አረጋግጠውላቸዋል።