የጃፓን ብሔራዊ ቡድን የእስያ ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚነቱን አረጋግጧል
17ኛው የእስያ ዋንጫ በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች አዘጋጅነት ከጥር 5/2019 ጀምሮ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
በ24 ቡድኖች መካከል እየተካሄደ የሚገኘው ውድድር ግማሽ ፍፃሜ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ በትናንትናው ዕለት አንድ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ የተከናወነ ሲሆን በሀዛ ቢን ዛይድ ስታዲየም ጃፓን ኢራንን 3 ለ 0 በመርታት የፍፃሜ ተፋላሚ መሆኗን አረጋግጣለች፡፡
ኢራን ለፍፃሜ አለማለፏ ከተረጋገጠ በኋላ ብሔራዊ ቡድኑን ለላፉት ስምንት ዓመታት ያሰለጠኑት አሰልጣኝ ካርሎስ ኪሮዥ መለያየታቸው ተነግሯል፡፡
ለጃፓን ጎሎቹን ኦሳኮ ሁለት ሲያስቆጥር እና ሀራጉቺ ቀሪዋን ግብ ከመረብ አገናኝቷል፡፡
ሌላኛው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ደግሞ ዛሬ ሲካሄድ ኳታር በመሀመድ ቢን ዛይድ ስታዲየም ከአዘጋጇ የተባበሩት አረብ ኤመሬቶች ጋር በ11፡00 ትፋለማለች፡፡
ኳታር የሰን ሁንግ ሚንን ሀገር ደቡብ ኮሪያ እንዲሁም የተባበሩት አረብ ኤመሬቶች አውስትራሊያን በተመሳሳይ 1 ለ 0 አሸንፈው በፖለቲካው ያለውን ቁርሾ ወደ ጎን ብለው ይሄንን ጨዋታ ያከናውናሉ፡፡
የኳታር እና የተባበሩት አረብ ኤመሬቶች ግጥሚያ አሸናፊ ከጃፓን ጋር በመጭው የካቲት 1/2019 አቡ ዳቢ ላይ በተገማሸረው የዛይድ ስፖርትስ ሲቲ ስታዲየም ይፋለማሉ፡፡
የውድድሩን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት የኳታሩ አጥቂ አልሞኤዝ አሊ በ7 ጎሎች እየመራ ይገኛል፡፡