32ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ የካቲት 11 እንደሚጀመር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት ከየካቲት 7 እስከ 8 የሚኒስትሮች ስብሰባ የሚካሄድ መሆኑን ገልፀው ከየካቲት 10 እስከ 11 ድረስ ደግሞ የመሪዎቹ ስብሰባ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በ32ኛው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ወቅት የአፍሪካ ህብረት ተቋማዊ ሪፎርምን በተመለከተ በጥልቀት ውይይት የሚደረግበት እና የወቅቱ የህብረቱ ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜን ጨምሮ ዋና ፀሃፊው ሙሳ ፋቂ መሀመት የአፈፃፀም ሪፖርታቸውን የሚያቀርቡበት ነው ተብሏል።
በጉባኤው ላይ ከሌሎች ጊዜያቶች በተለየ የአፍሪካ እና የኢትዮጵያ አርቲስቶች አፍሪካን በሚያጎላ መልኩ ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት እና አፍሪካዊ ትዕይንቶች የሚቀርቡበት እንዲሆን ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ሀላፊው ተናግረዋል፡፡