የኢል ክላሲኮ ጨዋታ ዛሬ ምሽት በኮፓ ዴል ሬይ ዋንጫ ይከናወናል
የስፔን ንጉስ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ ምሽት ይከናወናሉ፡፡
ዛሬ ምሽት 5፡00 ሲል ባርሴሎና በኢል ክላሲኮ ደርቢ ግጥሚያ ሪያል ማድሪድን ካምፕ ኑ ስታዲየም ላይ ያስተናግዳል፡፡ ይህ ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች በ25 ቀናት ውስጥ ከሚያከናውኗቸው፤ ሶስት የኢል ክላሲኮ ግጥሚያዎች አንዱ ነው፡፡
በዛሬው ፍልሚያ የባርሴሎናው አምበል ሊዮኔል ሜሲ ባለፈው ቅዳሜ ከቫሌንሲያ 2 ለ 2 አቻ በተለያየበት የላሊጋ ጨዋታ ጉዳት የገጠመው ቢሆንም ትናንት ልምምድ ጀምሯል ተብሏል፡፡
ሜሲ ከጨዋታው ውጭ ይሆናል ተብሎ ቢነገርም ክለቡ ለምሽቱ ግጥሚያ ካስመዘገባቸው 18 ተጫዋቾች ስም ዝርዝር አንዱ ሁኖ ተካትቷል፡፡
አሰልጣኝ ኢርኔስቶ ቫልቬርዴ ‹‹ አንዳንድ ጊዜ በተጫዋቾች ላይ ስጋቶች ይኖራሉ ይህ እውነታ ነው፤ እናም እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ድረስ ምን ሊሆን እንደሚችል መጠበቅ ይኖርብናል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
‹‹ይሄም ሜሲ ጋርም ይሰራል›› ሲሉ አክለዋል፡፡
አጥቂው ኦስማን ዴምቤሌ ከቋንጃ ጉዳቱ ያላገገመ በመሆኑ ከኢል ክላሲኮው ፍልሚያ ውጭ ሁኗል፡፡
በሪያል ማድሪድ በኩል ከተከላካዩ ሄሱስ ቫሊዬሆ ውጭ ሁሉም ተጫዋቾች ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው ተብሏል፡፡
በኢል ክላሲኮ 25 ጎሎችን በማበርከት ከፍተኛ ግብ ያስቆጠረውን ሊዮኔል ሜሲ እና ክርስቲያኖ ሮናልዶን ባላካተተው የጥቅምት ወር የላሊጋ ጨዋታ፤ የካታላኑ ቡድን በሊዩስ ሱዋሬዝ ሀትሪክ ግቦች ታጅቦ 5 ለ 1 መርታቱ ይታወሳል፡፡
በዛሬውም ጨዋታ ሜሲ የማይኖር ከሆነ ሁለቱን ኮከቦች በተከታታይ ሁለት ግጥሚያዎች ያላሳተፈ የኢል ክላሲኮ ፍልሚያ ይሆናል፡፡
ባርሴሎና የባለፉት አራት ዓመታት የኮፓ ዴል ሬይ የአራት ዓመታት ስኬት ዘንድሮ ያስቀጥል ይሆን፤ ወይስ በባላንጣው ክለብ ይሰናከልበት ይሆን የምሽቱ ጨዋታ ደግሞ ለዚህ ምላሽ ፍንጭ ይሰጣል፡፡
በነገው ዕለት ሪያል ቤቲስ በቤኒቶ ቪያማሪን ከ ቫሌንሲያ ይገናኛሉ፡፡