የምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እያወያየ ነው
ቦርዱ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚኖረውን ግንኙነት እና በተናጠል የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የሚገዛ የአሰራር ስርአት ቃል ኪዳን እና መርሆችን የያዘ ሰነድ እና አጀንዳ አዘጋጅቶ ነው ፓርቲዎችን እያወያ ያለው፡፡
በሰነዱ ፓርቲዎች ህገ መንግስቱን መሰረት ባደረገ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ፣
ሃይልን መጠቀም የመንግስት ብቻ ስልጣን መሆኑን ፣ የፓርቲ አመራሮች እና አባላት ወይም ደጋፊዎች በምንም ሁኔታ ህግን የማስፈፀም ስራ ውስጥ መግባት እንደማይችልም በውይይቱ ተነስቷል።
ሚዲያ እና የማህበራዊ ድረገፆች አጠቃቀም ላይም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚዲያ ተቋማትን ነፃነት እንዳይጋፉ ፣በፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ በደጋፊዎቻቸው ባለቤትነት የሚተዳደሩ የማህበራዊ ድረ ገፆች እና የህትመት ውጤቶች ማህበራዊ ጥላቻን፣ መቃቃርን፣ አመፅን፣ እና ህገ ወጥ ድርጊቶችን የማደፍረስ ውጤት ያላቸው መልዕክቶችን ከማስተናገድ እንዲቆጠቡ የማድረግ ሃላፊነት አለባቸው የሚሉ ሃሳቦች በቃል ኪዳን ሰነዱ ተካተዋል።
የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርትኳን ሚደቅሳ ህጉ አንድ መልክ ይዞ ከመውጣቱ በፊት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም ተወያይተው በሰነዱ እንዲካተት የተነሱ አጀንዳዎችንም ያካተተ እና በፓርቲዎች መካከል የሚኖረውን ግንኙነት እና የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የሚወስን ሰነድ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በውይይቱ የተገኙ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ቦርዱ ባቀረበው ሰነድ ውስጥ ፓርቲዎች እንዲካተቱ ያቀረቧቸው እና ያልተካተቱ አጀንዳዎች እንዳሉ አንስተዋል፡፡ የፓርቲዎቹ ውይይት የቀጠለ ሲሆን ማምሻውን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።