የመማር ማስተማሩ ሂደት ተቋርጦ የነበረው የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከፊታችን ሰኞ የካቲት 4 ጀምሮ ተማሪዎች ተመልሰው ትምህርት እንዲጀምሩ በሴኔት መወሰኑን ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ ።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ እንደተናገሩት የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር እና መምህራን ትናንት ከተማሪ ወላጆች ጋር ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ ሴኔቱ ተማሪዎች ወደ ትምህርት እንዲመለሱ ወስኗል ብለዋል።
ከተማሪ ወላጆች ጋር በተደረገ ውይይትም ወላጆች ተማሪዎች ጥያቄ ቢኖራቸውም ትምህርት ማቋረጣቸው ተቀባይነት የሌለው መሆኑንና የተፈጠረው ችግርም እንዳሳዘናቸው መናገራቸውን አንስተዋል።
ወላጆች ለተማሪዎቹ ድርጊት ይቅርታ እንዲደረግ መጠየቃቸውን ተከትሎም ሴኔቱ ያስተላለፈውን የአንድ ሴሚስተር ቅጣት ማንሳቱን ገልጿል።
የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ትምህርት ማቆማቸውን ተከትሎ ከጥር 12 ቀን እስከ 14 ቀን 2011 ዓ.ም ጊቢውን ለቀው እንዲወጡ መደረጋቸው ይታወሳል ። ዘገባው የፋና ነው።