ባለፉት 7 ወራት ኢትዮጵያ ወደውጭ ከላከቸው ቡና ያገኘችው የውጭ ምንዛሬ መጠን በ56 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል ተባለ
በሰባቱ ወራት ወደውጭ ገበያ ለመላክ ከታቀደው ከ16 ሺህ 546 ቶን ቡና ውስጥም መላክ የተቻለው 11ሺህ 165 ቶን መሆኑ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አንደሚጠቁመው በ2011 በጀት ዓመት ጥር ወር 16 ሺህ 5 መቶ 46 ቶን የቡና ምርት በመላክ 59 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እንደነበር ገልጿል፡፡
ከዚህም ውስጥ 11ሺህ 1መቶ 65 ቶን ቡና በመላክ 33 ነጥብ 66 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡
በመሆኑም ባለስልጣኑ በዕቅድ ይዞት ከነበረው የገቢ እቅድ የ56 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱ ተመልክቷል፡፡
አፈፃፀሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠን ከ13 በመቶ በላይ ቅናሽ አሳይቷል፡፡
ባለስልጣኑ በቡና እና ሻይ ቅመማ ቅመም የውጭ ንግድ ደግሞ ከባለፈው አመት ጋር ተመሳሳይ አፈፃፀም ማሳየቱን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
በ2011 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሰባት ወራት ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሀገራት ከላከችው ቡና በመዳረሻ ሀገራት የተገኘው ገቢ ሲታይ ከሳውዲ አረቢያ የተገኘው 71 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡
በነዚሁ መዳረሻ ሃገራት ገቢ አንጻር ሲታይ ጀርመን ከኢትዮጵያ በገዛችው በ50 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ቡና ስትከተል ጃፓን 43.96 ሚልዮን የአሜሪካን ዶላር በማስገኘት ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸውን ነው ሪፖርቱ የሚያመላክተው፡፡
በተመሳሳይም በ2011 በጀት አመት ሰባት ወራት የሻይ ምርት የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከእቅዱ በታች የሆነ ገቢ መገኘቱን ነው ሪፖርቱ የሚጠቁመው።
በ2011 በጀት ዓመት የጥር ወር 270 ቶን የሻይ ምርት በመላክ 650 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም የተላከው የሻይ ምርትም ይሁን የተገኘው ገቢ ከታቀደው በታች ሆኖ መመዝገቡን ሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል። በዚህም መሰረት ከሻይ ምርት የውጭ ንግድ የተገኘው ገቢ 300ሺህ የአሜሪካን ዶላር ብቻ ሆኗል።ያለፈው አመት የጥር ወር ገቢ ከዚህ የተሻለ እንደነበር ያመለክታል ሪፖርቱ።