በኢሮፓ ሊግ ታላላቅ ክለቦች ቀጣዩን ዙር ተቀላቅለዋል
የ2018/19 የኢሮፓ ሊግ በ32 ቡድኖች መካከል የሚደረገው የጥሎ ማለፍ የመልስ ግጥሚያዎች ተካሂደዋል፡፡
ትናንት ምሽት በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች በርካታ ጨዋታዎች የተከናወኑ ሲሆን፤ አርሰናል በኤመሬትስ የቤላሩሱን ባቴ ቦሪሶቭ አስተናግዶ 3 ለ 0 ሲረታ፤ በአጠቃላይ ደግሞ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፎ 16ቱን የጥሎ ማለፍ ተፋላሚ ክለቦች ተቀላቅሏል፡፡
ለመድፈኞቹ የድል ጎሎችን የባቴው ቮልኮቭ በራሱ መረብ ላይ፣ተከላካዮቹ ሙስታፊ እና ፓፓስታቶፑሎስ ደግሞ ቀሪዎቹን ከመረብ አገናኝተዋል፡፡
ሌላኛው የእንግሊዝ ቡድን ቼልሲ ስታንፎርድ ብሪጅ ላይ የስዊድኑን ማልሞ ገጥሞ በተመሳሳይ 3 ለ 0 ሲያሸንፍ፤ በድምር ውጤት 5 ለ 1 ድል በማድረግ ቀጣዩን የጥሎ ማለፍ ዙር ተዋህዷል፡፡
በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ግብ ያልተቆጠረ ሲሆን በሁለተኛው ግን ሰማያዊዎቹ በኦሊቪዬ ዥሩ፣ ሮዝ ባርክሌይ እና ካሉም ሁድሰን- ኦዶይ ግቦች ፈንጥዘዋል፤ የማውሪዚዮ ሳሪ ጫናም በመጠኑ እየረገበ ይገኛል፡፡
በሌሎች በተደረጉ የደርሶ መልስ ግጥሚያዎች ኢንተር ሚላን፣ ናፖሊ፣ ቫሌንሲያ፣ ቪያሪያል፣ ቤንፊካ፣ አይንትራክት ፍራንክፉርት፣ አር.ቢ ሳልዝበርግ፣ ዲናሞ ዛግሪብ፣ ዜኒት ፒተርስበርግ፣ ዳይናሞ ኬቭ፣ ክራስኖዳር፣ ስላቪያ ፕራህ፣ ሬን እንዲሁም አስቀድሞ ማለፉን ያረጋገጠው ስቪያ በተጋጣሚያቸው ላይ የበላይ በመሆን በኢሮፓ ሊግ round of 16 ጥሎ ማለፍ ተፋላሚነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
የጥሎ ማለፉ የዕጣ ድልድል በዛሬው ዕለት ከቀትር በኋላ ኒዮን ሲውዘርላድ ላይ ይፋ ይሆናል ተብሏል፡፡