በምሳ ሰዓት እንማማር” የተሰኘውና በጤና ሚኒስቴር የተዘጋጀው የምሣ ሰዓት የመማማሪያ ኘሮግራም ተካሄደ፡፡
በኘሮግራሙ ላይ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትሮች፤ ዳይሬክተሮች፣ ረዳት ዳይሬክተሮች እና የተጠሪ ተቋማት አመራሮች የተገኙ ሲሆን የዚህ ዓይነቱ ኘሮግራም መዘጋጀቱ ለዕርስ በርስ መማማርና ልምድ መለዋወጥ አጋዥ እንደሚሆን የገለጹት በዕለቱ ስለ “Learning organization” አጠር ያለ ገለፃ ያቀረቡት ጤና ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን ናቸው፡፡
ኘሮግራሙ ያስፈለገው ተከታታይነት ያለው የመማማሪያ መድረክ ለመፍጠር፣ የተሻለ ልምድ ካላቸው ትምህርት ለመቅሰም እና በውስጥ ለውስጥ ቅንጅት አዳዲስ የመማማሪያ ባህሎችን ለመገንባት እንደሆነ የጠቀሱት ዶ/ር አሚር ሁልጊዜም በድፍረት ለመማር ዝግጁ የሆነ ሰው የሚፈልገውን አዳዲስ ዕውቀት ለማግኘት አይቸገርም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የአንድ ሰው አዕምሮ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ለመማር እና ለማወቅ ፍላጎትና ችሎታ እንደተካነ የቅርብ ጊዜ ጥናቶችን ዋቢ አድርገው የገለፁት ሚኒስትሩ ትምህርት በሁሉም ስፍራ እንደሚገኝ የተረዳ ሰው ዕድሜውን ሙሉ የማይዘረፍ የዕውቀት ሃብት ለማከማቸት ዘወትር መትጋት አለበት ብለዋል፡፡
በቀጣይ በሚከናወኑ የመማማር መድረኮች አዳዲስ የስራና የፈጠራ ሃሣቦች ከታች ወደላይ እንዲዘልቁና ሥራዎች እንዲከናወኑ እንደሚፈለግ ጭምርም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በቅንጅታዊ የመማማር ሂደት መሰረት ደጋፊ የአመራር ሰጪነትን መካን፣ የስራን ውድቀትና ዕድገት ሁሌም የመገምገም ባህልን ማዳበር ሥራን በብልሃትና በአስተውሎት ለመምራት ዘወትር መዘጋጀት፣ ሁሌም ማቀድና ለለውጥ ዝግጁ መሆንና የመሣሠሉትን በትኩረት መገንዘብ እንደሚገባ የገለፁት ሚኒስትሩ በየሣምንቱ ለሚከናወነው ኘሮግራም ምን አዲስ ነገር ከሌሎች ተማርን? ምንስ አዲስ ነገር ለሌሎች አስተማርን በሚለው ላይ ሣምንቱን ሁሉ አስበንበት እንቅረብ ብለዋል፡፡
የዚህ ዓይነቱ ኘሮግራም ባደጉት አገራት በአብዛኛው የተለመደ መሆኑን የገለፁት በጤና ሚኒስቴር የሰው ሃብት ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ የዕለቱን የመጀመሪያ በምሳ ሰዓት የመማማር መድረክ ያስተባበረው የሰው ሃብት ልማት ዳይሬክተር መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ሌሎች ዳይሬክቶሬቶችና ተጠሪ ተቋማት የማስተባበሩን ሚና በየተራ ይወጣሉ ብለዋል፡፡
በኘሮግራሙ ላይ በእንግድነት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ዶ/ር ምህረት ደበበ በበኩላቸው ሰው በሥራ ዘመኑ እየተማረ ወይም እየከሰረ እንደሚሄድ ይታወቃል ካሉ በኋላ የዚህ ዓይነቱ መድረክ በጤና ሚኒስቴር መዘጋጀቱ ለእርስ በርስ መማማር ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡
“በምሳ ሰዓት እንማማር” ” የተሰኘው የመማማሪያ መድረክ ዘወትር ሐሙስ በምሣ ሰዓት በጤና ሚኒስቴር አዳራሽ የሚከናወን መሆኑ ታውቋል፡፡