የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሙሀመድ አብዱላሂ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሙሀመድ አብዱላሂ ሙሀመድ “ፋርማጆ” ዛሬ ጠዋት አዲስ አበባ ገብተዋል።
ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በአቀባበል ስነ ስርዓቱ ላይ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደክተር ወርቅነህ ገበየሁን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ተገኝተዋል።
ከዉጭጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት እንደገለጸዉ ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር በሁለትዮሽና በክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ያደርጋሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአፍሪካ ቀንድ ክልላዊ ሰላም ለማስፈንና የኢኮኖሚ ትስስርን ለማጠናከር የጀመሩት ዲፕለማሲያዊ እንቅሰቃሴ አካል በሆነው በዚህ ጉብኝት በክልሉና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚመክሩ ይጠበቃል።
ፕሬዝዳንት መሀመድ አብዱላሂ መሐመድ በኢትየጵያ በአንድ ቀን በሚኖራቸው ቆይታ ባላፉት ቀናት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከኬንያ ፕሬዝዳንት ኡህሩ ኬንያታ፣ ከኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እንዲሁም ከደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት ጋር ካደረጓቸው የሁለትዮሽና የሶስትዮሽ ውይይቶች የቀጠለ በቁልፍ ቀጣናዊና የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚወያዩ ይጠበቃል።