በዩሮፓ ሊግ የመጨረሻ 16ቱ ቡድኖች የጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ይከናወናሉ
ምሽት 2፡55 ላይ አምስት ጨዋታዎች የሚከናወኑ ሲሆን የእንግሊዙ አርሰናል ወደ ፈረንሳይ በማቅናት ከሬን ጋር በሮዞን ፓርክ ይፋለማል፡፡
መድፈኞቹ ከፈረንሳዩ ቡድን ሬን በኩል ብርቱ ፉክክር እንደሚገጥመው ይጠበቃል፡፡
የሬኑ አጥቂ ምባዬ እና ተከላካዩ ሃማሪ ትራኦሬ በቅጣት የማይሰለፉ ይሆናል፤
አሰልጣኝ ኡናይ ኢመሪ ወጣቱን ኤዲ ኒኪታህ በአሌክሳንደር ላካዜት ምትክ እንዲሰለፍ ወደ ፈረንሳይ ሬን ይዘውት ተጉዘዋል ተብሏል፡፡
ሬን አርሰናልን ሲገጥም በሁሉም የአውሮፓ ውድድሮች 10ኛው የፈረንሳይ ቡድን ሲሆን የእንግሊዙ ቡድን ከዚህ ቀደም የገጠማቸውን ሁሉንም ቡድኖች ድል አድርጓል፡፡
በተመሳሳይ ሰዓት የስፔኑ ሲቪያ በራሞን ሳንቼዝ ፒዡዋን የቼክ ሪፐብሊኩን ስላቪያ ፕራሃን፤ የጣሊያኑ ኢንተር ሚላን ወደ ጀርመን አቅንቶ ከአይንትራክት ፍራንክፉርት፤ የሩሲያው ዚነት ፒተርስበርግ የስፔኑን ቪያሪያል እንዲሁም የክሮሽያው ዲናሞ ዛግሪብ የፖርቱጋሉን ፖርቶ ይገጥማሉ፡፡
ምሽት 5፡00 ላይ ደግሞ ቀሪዎቹ ሶስት ጨዋታዎች ሲደረጉ ቼልሲ ስታንፎርድ ብሪጅ ላይ የዩክሬኑን ዳይናሞ ኬቭ ያስተናግዳል፡፡
የእንግሊዝ ክለቦች ላይ ያለውን የጨዋታዎች መደራረብ ላይ ትቻታቸውን ያሳረፉት የቼልሲው አሰልጣኝ ማውሪዚዮ ሳሪ ተጫዋቾቻቸው በአካልም በአእምሮም እንደደከሙ ተናግረዋል፡፡
የምዕራብ ለንደኑ ክለብ በ18 ቀናት ውስጥ ዛሬ ሰባተኛ ጨዋታቸውን የሚያደርግ ይሆናል፡፡
በዚህም ምክንያት ሳሪ የእንግሊዝ ክለቦች በአውሮፓ የውድድር መድረኮች ላይ ውጤት እንዳያስመዘግቡ መሰናክል እንደሚሆንባቸው ጠቁመዋል፡፡
ቅድሚያ የማሸነፍ ዕድል የተሰጠው ለእንግሊዙ ቡድን ቢሆንም የዩክሬኑ ቡድን አሰልጣኝ ኦሌክሳንደር ሄትኬቪች ግን ‹‹ የማሸነፍ ዕድል ግምቱ ወረቀት ላይ ብቻ የሚሰፍር ነው፤ ከጨዋታ በፊት የሚሰጡት ግምቶች 50 -50 ብቻ ናቸው ብለዋል፡፡
አክለውም ለአሁኑ ለመናገር የተዘጋጀሁት ነገር ቢኖር ቼልሲዎች ሰማያዊ ማሊያ እንደሚለብሱ ነው ሲሉ ስለአሁናዊ የተጋጣሚያቸው ወቅታዊ ብቃት ተናግረዋል፡፡
እንደ ሳሪ አባባል በቡድናቸው በኩል ምንም አይነት ጉዳት እንደሌለ ነገር ግን ሮዝ ባርክሌይ በተመለከተው ካርድ ቅጣት እንዳለበት ተነግሯል፡፡
በምሽቱ ሌሎች ግጥሚያዎች በተመሳሳይ ሰዓት ሲደረጉ፤ የጣሊያኑ ናፖሊ በሳን ፓውሎ ስታዲየም የኦስትሪያውን ሬድ ቡል ሳልዝበርግ ሲያስተናግድ፤ የስፔኑ ቫሌንሲያ ሜስቲያ ላይ የሩሲያውን ክራስኖዳር ይገጥማል፡፡