በአየር መንገዱ ተጓዦች ላይ በደረሰው አደጋ የተለያዩ የስፖርት ተቋማት ሀዘናቸውን እየገለፁ ነው
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነ ቦይንግ 737 በረራ ቁጥር 302 ትናንት ጠዋት ከአዲስ አበባ ተነሥቶ ወደ ኬንያ ናይሮቢ ይበር የነበረው አውሮፕላን፤ ደብረ ዘይት አካባቢ በገጠመው የመከስከስ አደጋ ኢትዮጵያዊያን ዜጎችን ጨምሮ በአደጋው የ35 ሀገራት 157 ዜጎች ህይወት አልፏል፡፡
የሀገር ቤት እና የባህር ማዶ ስፖርታዊ ተቋማትም በአደጋው የተሰማቸውን ሀዘን እየገለፁ ነው ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 የሆነዉ አዉሮፕላን ትናንት ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ በመብረር ላይ እንዳለ በደረሰበት አስከፊ የመከስከስ አደጋ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተሰማንዉን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ በዚህ አደጋ ህይወታቸዉን ላጡ ወገኖች ሰላማዊ እረፍትን ለቤተሰቦቻቸዉ ደግሞ መጽናናትን ይመኛል ሲል በፌስቡክ ገፁ ላይ ሀዘኑን ገልጧል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዚህ ልብ ሰባሪ ክስተት ጥልቅ ሃዘን እንደተሰማው እና ህይወታቸውን ላጡ ተጓዦችና ቤተሰቦች ፈጣሪ ፍፁም መፅናናትን ይሰጥ ዘንድ ይመኛል ሲል በፌስቡክ ገፁ ላይ እና ለአርትስ በላከው መግለጫ አስፍሯል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም በአደጋው የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልፆ፤ ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦችና ለመላው ኢትዮጵያውያን መፅናናትን ይመኛል ሲል ፌዴሬሽኑ በፌስቡክ ገፁ ላይ እና ለአርትስ በላከው መግለጫ አስፍሯል፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በቲውተር ገፁ እንዳስታወቀው በአውሮፕላን አደጋው፤ ከሟቾቹ መካከል ኬንያዊ የካፍ ኮሚሽነር ሁሴን ስዋሌህ ምቴቱ አንዱ እንደሆነ አስታውቆ የካፍ ፕሬዚዳንት አህመድ አህመድ ለሁሴን ስዋሌህ ምቴቱ ቤተሰቦች፣ ዘመዶችና ለኬንያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ባለፈው አርብ አሌክሳንድሪያ ላይ በግብፁ እስማይሊ እና በዲ.ሪ.ኮ ቲፒ ማዜንቤ የተደረገውን የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ከመሩ በኋላ ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ በነበረበት ወቅት ነው አደጋው የደረሰው፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባወጣው የሟቾች ቁጥር እና ዜግነት ዝርዝር ውስጥ፤ የሁለት ስፔናዊያን ዜጎች ህይወት ያለፈ ሲሆን የስፔን የላሊጋ አስተዳዳሪ አካል በፌስቡክ ገፁ እንዳስቀመጠው፤ አዲስ አበባ አቅራቢያ በተከሰከሰው የአውሮፕላን አደጋ ለተጎጂ ዜጎች፣ ቤተሰቦቻቸው እና ለሁሉም መፅናናትን ተመኝቷል፡፡
ከሌላኛዋ የአውሮፓ ሀገር ጣሊያን ደግሞ የ8 ዜጎች ህይወት ሲቀጠፍ የሀገሪቱ ዋና ከተማ ክለብ ኤ.ኤስ ሮማ በቲዊተር ገፁ እንዳሰፈረው በኢትዮጵያ አየርመንገድ የአውሮፕላን መከስከስ አደጋ እና ተጓዥ ዜጎች ላይ በደረሰው ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ የሆነ ሀዘን ገልፆ፤ ለተጓዦችና የበረራ ሰራተኞች ቤተሰቦቻቸው እና ጓደኞቻቸው መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡
አርትስ ስፖርትም በደረሰው አደጋ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ፤ ፈጣሪ ለሟች ወገኖች አፀደ ገነትን እንዲያወርስ፤ ለተጎጂ ቤተሰቦችና ወዳጆች ደግሞ መፅናናትን እንዲሰጥ ይመኛል፡፡