Uncategorized

የአልጄሪያው ፕሬዝዳንት አብደላዚዝ ቡተፍሊካ በቀጣዩ ምርጫ እንደማይሳተፉ አስታወቁ

ፕሬዝዳንቱ ለአምስተኛው ዙር የአልጄሪያ ምርጫ እሳተፋለሁ ማለታቸው በሃገሪቱ ከፍተኛ ረብሻ እና ተቃውሞ ቀስቅሶ ነበር፡፡

የ82 ዓመቱ ፕሬዝዳንት አብዱላዚዝ ቡተፍሊካ ለአምስተኛ ጊዜ ለፕሬዝዳንትነት እንደሚወዳደሩ ማሳወቃቸውን ተከትሎ በአልጄሪያ  ከፍተኛ ተቃውሞ እና ውግዘት ደርሶባቸው ነበር።

በምርጫው ተወዳድሬ ባሸንፍም  ከአንድ ዓመት በላይ ስልጣን ላይ የመቆየት ፍላጎትም አቅምም የለኝም ቢሉም ለተቃውሞ የወጡት ህዝቦች ግን የለም ለ20 ዓመታት አልጀሪያን ያስተዳደራት የቡተፍሊካ መንግስት ተቀይሮ አዲሲቷን አልጄሪያ የሚመሰርት አዲስ አስተዳደር ነው የምንፈልገው ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

ለ20 ዓመታት በስልጣን የቆዩት ፕሬዝዳንቱ ከባድ የጤና እክል ካጋጠማቸው ሰነባብቷል።

ሮይተርስ እንዳስነበበው ከፈረንጆቹ 2013 ጀምሮም ባጋጠማቸው ከባድ የደም ግፊት ምክንያት ከህዝብ ርቀው ነበር፡፡

በሚያዚያ ወር እንዲካሄድ ፕሮግራም ተይዞለት የነበረው ምርጫውም ላልተወሰነ ጊዜ  ተራዝሟል፡፡

ከመንግስታቸው  የወጣው ለአምስተኛ ጊዜ አልወዳደርም የሚለው መግለጫቸው በቅርቡ የካቢኔ ሹም ሽር እንደሚደረግ ያትታል።

ቡተፍሊካ መግለጫው ላይ እንደጠቀሱት  ከጤናዬ እና ከእድሜዬ አንፃር በምርጫው እንደማልወዳደር ሳይታለም የተፈታ ነው፣ በመጨረሻም ለአልጀሪያውያን ማድረግ የምፈልገው ለአዲሲቷ ለሚፈጥሯት አገር መሰረትን መጣል ነው ብለዋል።

መግለጫው ፕሬዚዳንቱ ከምርጫው በፊት ስልጣን ይለቁ ይሆን ወይ ለሚለው ዝርዝር መረጃ አላወጣም።

አፍሪካን ኒውስ እንደዘገበው ፕሬዚዳንቱ ትናንት ማምሻውን  በምርጫ እንደማይሳተፉ መግለፃቸውን ተከትሎ ተቃዋሚዎች በአልጀሪያ ጎዳናዎች ላይ በመውጣትያካሄድነው  ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ  ትግል  በአጭር ጊዜ  ፍሬ አፍርቷል ሲሉ ደስታቸውን ገልፀዋል ።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር አህመድ ኡሃያ ስልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ኑረዲን ቤዱ እንደተኳቸው ተዘግቦ ነበር።

ኑረዲን ቤዱም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2014 በሀገሪቱ በተካሄደው ምርጫ አሸንፈው በ1999 የተረከቡትን ስልጣን ሲያስቀጥሉ በቴሌቭዥን መስኮት ብቅ ብለው መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከዚያን ቀን በኋላ ግን የውሃ ሽታ ሆነው ቀርተዋል። ሀገሪቱም በማይታይ ጠቅላይ ሚኒስትር እየተመራች ነው ሲሉ ተቃዋሚዎች ያነሳሉ፡፡

Show More

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button
Close
Close
Close Bitnami banner
Bitnami