በቻምፒዮንስ ሊግ ዛሬ ምሽት ባየርን ሙኒክ ከ ሊቨርፑል የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል
የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የመጨረሻ 16 ቡድኖች ወደ ሩብ ፍፃሜ ለመግባት በሚያደርጉት የዙር ፍልሚያ ዛሬ ምሽት ሁለት ተጠባቂ የመልስ ግጥሚያዎች በተመሳሳይ ምሽት 5፡00 ሰዓት ላይ ይከናወናሉ፡፡
የእንግሊዙ ሊቨርፑል ወደ ጀርመን አምርቶ በአሊያዝ አሬና ከባየርን ሙኒክ ይፋለማል፡፡ በጨዋታው ከእንግዳው ሊቨርፑል በኩል በመጀመሪያው ጨዋታ ያልተሰለፈው ቨርጂል ቫን ዳይክ የሚሰለፍ ሲሆን ጀምስ ሚልነር ከጡንቻ ጉዳቱ አገግሞ ሊሰለፍ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ጊኒያዊው አማካይ ናቢ ኬይታ ግን በቀላል ጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጭ ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል፡፡
በሙኒክ በኩል ጆሹዋ ኪሚች እና ቶማስ ሙለር በቅጣት ምክንያት ለቡድኑ ግልጋሎት የማይሰጡ ቢሆንም ተከላካዩ ዳቪድ አላባ እና የክንፍ መስመር ተሰላፊው ኪንግስሊ ኮማን ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው ተብሏል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያውን ፍልሚያቸውን ያለግብ በአቻ ውጤት ያጠናቀቁ ሲሆን በመልሱ ሙኒኮች ጀርመንን የወከሉ ብቸኛ የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ቡድን በመሆናቸው፤ ቀያዮቹ ደግሞ ሩብ ፍፃሜውን አስቀድመው የተቀላቀሉ የእንግሊዝ ቡድኖች ጋር ለመመሳሰል ሲሉ የጨዋታው ግለት ይንራል፡፡
ሌላኛው ግጥሚያ ስፔን ካታላን ግዛት ላይ ሲከናወን ባርሴሎና የፈረንሳዩን ሊዮን ያስተናግዳል፡፡
ከሳምንታት በፊት በተከናወነው የመጀመሪያው ግጥሚያ ባርሳ 25 የሚሆኑ የግብ ሙከራዎችን አድርጎ አንዱም ወደግብነት አልተቀየሩም፡፡
የካታላኑ ቡድን ዛሬ ምሽትም ሜዳው ላይ የሚጫወት ቢሆንም ከሊዮን በኩል የሚመጣው ፍልሚያ ቀላል አይሆንም ተብሏል፡፡
የባርሳው ኦስማን ዴምቤሌ ጉዳት ላይ በመሆኑ ቫልቬርዴ ለፊሊፔ ኮቲንሆ ቅድሚያ የመሰለፍ ዕድል እንደሚሰጡት ይጠበቃል፡፡
እስከ አሁን ባለው ሩብ ፍፃሜው ላይ የደረሱ ክለቦች ቀጥር ስድስት የደረሱ ሲሆን ቶተንሃም፣ ማንችስተር ዩናይትድ፣ አያክስ፣ ፖርቶ፣ ዩቬንቱስ እና ማንችስተር ሲቲ ናቸው፡፡
የቻምፒዮንስ ሊጉ የሩብ ፍፃሜ የዕጣ ማውጣት ድልድል ሰነ ስርዓት በመጭው አርብ ይካሄዳል፡፡