Uncategorized

አዳዲሶቹ የቦይንግ ምርቶች እገዳ እየበዛባቸው ነው

አዳዲሶቹ የቦይንግ ምርቶች እገዳ እየበዛባቸው ነው

እንግሊዝ ፣ፈረንሳይ፣ ጀርመንና አውስትራሊያ ቦይንግን ከበረራ ካገዱት ሃገራት ተቀላቅለዋል፡፡

ሀገራቱ ይህን እንዲወስኑ ያደረጋቸውም በኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ ማክስ 8 አውሮፕላንን መከስከስ ተከትሎ በዚህ አውሮፕላን ላይ የደረሰው አደጋ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ሁለተኛው የቦይንግ አውሮፕላን በመሆኑና በአደጋዎቹ የብዙ ሰዎች ሕይወት በመጥፋቱ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ  የኖርዌይ፣ የብራዚል እና የኦማን ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን መስሪያ ቤቶችም ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላኖች ከበረራ አገልግሎት ውጪ እንዲሆኑ ትእዛዝ አሳልፈዋል።

ነገሮችን ከቅርብ ሲቆጣጠር የነበረው የእንግሊዝ ሲቪል አቬሽን  ለጊዜው ከመረጃ ሳጥኑ በቂ መረጃ ባለመገኘቱ ለጥንቃቄ ሲባል አውሮፕላኖቹን ከማብረርም ሆነ በእንግሊዝ ከባቢ አየር እንዳይበሩ አግደናል የሚል መግለጫ አውጥቷል።

የኖርዌይ አየር መንገድም የዚህን አውሮፕላን በረራዎች በሙሉ አግዷል፡፡በቢሾፍቱ አካባቢ የተከሰከሰው ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን   ከ10-12 ከመቶ ነዳጅ ቆጣቢ እንደሆነ እና ዘመናዊ በሆነ መንገድ ተሻሽሎ እንደመጣ ይነገርለታል። የዚህ አውሮፕላን ሥሪት በቦይንግ ታሪክ ብዙ ገበያን ያገኘና በ737 ሞዴሎች ዝርዝር ውስጥ የመጨረሻውና እጅግ ዘመናዊው መሆኑም ተነግሯል።

አውሮፕላኑ ወደ ገበያ የገባውም እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2016 ነበር። በእነዚህ ሁለት የአገልግሎት ዓመታት ውስጥ ታዲያ አውሮፕላኑ ሁለት ጊዜ አደጋ አጋጥሞታል። አውሮፕላኖቹ በተነሱ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ መከስከሳቸው ሁለቱን አደጋዎች እንደሚያመሳስላቸው እየተነገረ ይገኛል፡፡

የአደጋው መንስኤ ምርመራ ተደርጎ በሲቪል አቬሽን ባለሥልጣን እስኪገለፅ እንዲህ ነው፣ እንዲያ ነው ብሎ መገመትን ዓለም አቀፉ የሲቪል አቬሽን ድርጅት ስለሚከለክል የመቆጠብ ነገር ቢኖርም ጣቶች ወደ ቦይንግ ኩባኒያ የተቀሰሩ ይመስላል፡፡

ዓለም ዓቀፍ የአቬሽን ኤክስፐርቶችም በስፋት እየገለጹ ያሉት የአውሮፕላኑ የበረራ መቆጣጠሪያ ስሪቱ አንዳች ችግር ሳይኖረው አይቀርምና እሱ ላይ ትኩረት ተደርጎ ምርመራ መደረግ እንዳለበት ነው፡፡

በአሁኑ ሰዓት በርካታ ግዙፍ አየር መንገዶችም ይህንኑ የቦይንግ ሥሪት ለጊዜው ከአገልግሎት ውጭ ማድረጋቸው  ይህንኑ የሚጠቁም ማሳያ ነው ይላሉ፡፡ኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ ብቻ ሳይሆን አሁን ከኤር ባስ ጋርም ደንበኝነት ጀምሯል፡፡

አዲስ አውሮፕላን ሲወጣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፓይለቶች አምራቹ ጋር ሄደው ስልጠና እንደሚወስዱ  የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገ/ማሪያም የኢትዮጵያ አየር መንገድ  የኤር ባስ ባለቤት በሆነበት ወቅት መናገራቸው ይታወሳል።

ቦይንግ 737 ማክስ 8 ሞዴል በ 6 ወር ጊዜ ውስጥ ሁለቴ የመከስከስ አደጋ ቢያጋጥበውም የአሜሪካ የፌደራል አየር መንገድ አስተዳደር ግን አውሮፕላኑ ለመብረር ብቁ ነው ሲል ማረጋገጫ ሰጥቷል።

የመረጃ ሳጥኑ መገኘት ይህን ብዥታ ለማጥፋት ሁነኛ መፍትሄ እንደሆነ ኤክስፐርቶች ይናገራሉ፡፡ የመረጃ ሰጪ ሳጥኑ እጅግ ረቂቅ በመሆኑ ምርመራ የሚደረገው ወደ ውጭ ተልኮ ነው።

የምርመራ ውጤቱ ከውስብስብ የአቪየሽን ፖለቲካ ነጻ ለማድረግም ከፍተኛ ጥንቃቄን ይፈልጋል። ይህም የሚሆነው አውሮፕላን አምራቾችን ጨምሮ አየር መንገዶች በውጤቱ ላይ  እጃቸውን እንዳያስገቡ ሲባል ነው፡፡

በዓለም አቀፉ የሲቪል አቬሽን ድርጅት አሠራር መሠረት የአደጋውን ምርመራ የመምራትና ምርመራ የማድረግ ሥልጣን አደጋው የደረሰበት አገር ሲቪል አቬሽን ባለሥልጣን ይሆናል።

ቤሩት ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ ሲደርስበት የምርመራውን ሂደት የመራው የሊባኖስ ሲቪል አቬሽን ባለሥልጣን እንደነበር ይታወሳል፡፡

 

Show More

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button
Close
Close
Close Bitnami banner
Bitnami