የአለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (IAAF) በዶሃ – ኳታር ተሰብስቦ እ.አ.አ. ከ2020 ዓ/ም የዲያመንድ ሊግ ውድድር ጀምሮ፤ የ5,000 ሜትር የሩጫ ውድድር ከዲያመንድ ሊግ መሰረዙን ከቀናት በፊት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የማህበሩ ካውንስል የወሰነውን ውሳኔ ተከትሎ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ተቃውሞውን ለአለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ፕሬዝደንት፣ ለአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን እና ለምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሪጅን አስታወቋል፡፡
የአለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ይህን ውሳኔ ያሳለፈው ዲያመንድ ሊግ የ10ኛ ዓመት የምስረታ ዘመኑን እያከበረ ባለበት ወቅት ሲሆን የአለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ዲያመንድ ሊግ ቦርድ እና ዳይሬክተሮች ውድድሩን የተሻለ ለማድረግ ከ2020 ጀምሮ የተለያዩ ማሻሻያዎች ላይ ውይይት ሲያደርግ ነው፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባወጣው ተቃውሞ የተላለፈው ውሳኔ፤ በፌዴሬሽኑ ላይ ድንጋጤን እንደፈጠረ፤ የማህበሩንም አባል ፌዴሬሽኖች ፍላጎት ያላገናዘበ እንዲሁም በጉዳዩ ላይ በቂ ጥናት ተደርጎበት የተላለፈ እንደሆነ ቢነገርም ምስራቅ አፍሪካን በጉዳዩ ላይ ያላካተተ ስራዎች መሰራታቸውን ጨምሮ ጠቅሷል፡፡
የረዥም ርቀት የሩጫ ውድድሮችን ከውድድር ማገድ ርቀቱን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ባህል እና መለያ የሚታይ በመሆኑ 5 ሺ የተላለፈው ውሳኔ እና 10 ሺ ላይ ያለው ሀሳብ ፍትሃዊ ያልሁነ በመሆኑ በድጋሜ እንዲታይ ሲል ደብዳቤውን ለማህበሩ ልኳል፡፡
በረዥም ርቀት የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊያን እና የጎረቤት ኬንያ አትሌቶች እንዲሁም ምስራቅ አፍሪካውያን የነገሱበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡