በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ላሉ 170ሺህ ስራ አጥ ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ያግዛል የተባለ የ2 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ጸደቀ።
ፈንዱን ያጸደቀው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ባካሄደው ስብሰባ ለወጣቶች ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ ለመመደብ የቀረበ ረቂቅ ሰነድ ላይ ተወያይቶ አፅድቋል፡፡
በዚህም መሠረት ዝርዝር ዕቅዶችን በማዘጋጀት እና ከወጣቱ ጋር ሰፊ የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት የጋራ መግባባት ላይ ከተደረሰ በኋላ ወጣቶቹ በተለያየ ዘርፍ ወደ ስራ እንዲገቡ የሚያስችል ነው የተባለ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
በከተማዋ ከ700ሺ በላይ ስራ አጥ ወጣት እንዳሉ መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን ይህ የሁለት ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ ይህንን የስራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ እና የከተማዋን ኢኮኖሚ በማነቃቃት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚኖረውም ይጠበቃል ሲል የከንቲባ ፅህፈት ቤት አስታውቋል፡፡