አዲሱ የአልጄሪያ ጠቅላይ ሚንስትር አዲስ ካቢኔ ላዋቅር ነው አሉ።
የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አህመድ ኦያሂያ በሀገሪቱ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ስልጣናቸውን መልቀቃቸው የሚታወስ ሲሆን እርሳቸውን ተክተው ኑረዲን ቤዶኡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ተሹመዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት የተሾሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ገለልተኛ የሆኑ ባለሙያዎችን ያካተተ አዲስ ካቢኔ ለመሰየም ውይይት ማድረግ መጀመራቸውን የሀገሪቱ ዜና ወኪል ኤፒኤስ ዘግቧል፡፡
አዲስ የሚቋቋመው ካቢኔ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ የሆኑ ባለሙያዎችን ያካተተ እና የህዝቦችን ውክልና ያረጋገጠ ይሆናልም ተብሎለታል፡፡
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አልጄሪያውያን ከሶስት ሳምንታት በላይ ባደረጉት ታላቅ ተቃውሞ ሀገሪቱን ለ20 ዓመታት በፕሬዜዳንትነት የመሩትን አብዱላዚዝ ቡቶፍሊካን የስልጣን ዘመን ወደ ማብቂያው እንዲሄድ አድርጎታል፡፡
የ82 ዓመቱ የእድሜ ባለጸጋ እና በተሽከርካሪ ወንበር የሚንቀሳቀሱት ፕሬዜዳንቱ ለአምስተኛ ዙር ከሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ራሳቸውን ማግለላቸውንና በቀጣዩ ወር ሊካሄድ የነበረውን ፕሬዜዳንታዊ ምርጫ ማራዘማቸውን አልጄዚራ ዘግቧል፡፡
በርካታ ተቃዋሚዎች ግን ውሳኔው የፕሬዜዳንቱን የስልጣን ዘመን ለማራዘም የታለመ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
እንደ አውሮውያን አቆጣጠር በ1990ዎቹ በሀገሪቱ ምርጫ ሊያሸንፍ ተቃርቦ የነበረው ኢስላሚስት ፓርቲ ውጤት መሰረዝን ተከትሎ የእርስ በእርስ ጦርነት ተቀስቅሶ ነበር፡፡
ከ ፈረንጆቹ1999 ጀምሮ በስልጣን የቆዩት ቡቶፍሊካ ሁለት መቶ ሺህ ዜጎችን ለህልፈት ከዳረገው እልቂት ሀገሪቱን ወደ ተረጋጋ ሁኔታ መመለስ ችለዋል እንደ ነበርም የሚታወስ ነው፡፡